በእስራኤል ‘ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ’ የተባለ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ

እስራኤል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላዊያን በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የተባለውን ሰላማዊ ሰልፍ ተቀላቅለዋል።

ለአስር ሳምንታት ያክል የዘለቀው ሰልፍ መንግሥት ሊያካሂድ ያቀደውን የሕግ ሥርዓት ማሻሻያ የሚቃወም ነው።

በቴል አቪቭ ጎዳናዎች 200 ሺህ ያክል ሰዎች ሰልፍ ሲወጡ በሃይፋም በተመሳሳይ በርካታ ሰዎች ድምፃቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።

የመንግሥት ዕቅድን የሚተቹ ሰዎች አዲሱ ሕግ ዴሞክራሲን ይገዳደራል ይላሉ።

ነገር ግን የቤንያሚን ኔታኒያሁ መንግሥት ማሻሻያው ለድምፅ ሰጪዎች ይጠቅማል ይላል።

የተቃውሞ ሰልፉ አዘጋጆች ቅዳሜ ዕለት 500 ሺህ ገደማ ሰዎች በመላ ሃገሪቱ ሰልፍ ወጥተዋል የሚል መረጃ ለቀዋል።

የእስራኤሉ ሃሬትዝ ጋዜጣ የተቃውሞ ሰልፉን “በእስራኤል ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ” ሲል ገልጦታል።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ዬር ላፒድ በደቡባዊቷ የቢር ሺቫ ከተማ ተገኝተው “ሃገሪቱ ታሪካዊ ቀውስ ውስጥ ናት” ሲሉ ለሰልፈኞች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

“ሽብርተኝነት እያጠቃን ነው። ምጣኔ ሃብታችን ተቃውሷል። ገንዘብ ከሃገር እየወጣ ነው። አራን ከሳዑዲ አራቢያ ጋር ስምምነት ገብታለች። ነገር ግን ይህ መንግሥት የሚያሳስበው የሃገሪቱን ዲሞክራሲ መደቆስ ነው” ብለዋል።

ቴል አቪቭ በነበረው ሰልፍ ተሳታፊ የነበረው ታሚር ጉይትሳብሪ “ማሻሻያው ብቻ ሳይሆን እየተካሄደ ያለው አብዮትም እስራኤልን ወደ ሙሉ አምባገነናዊ ሥርዓት እየወሰዳት ነው። ልጆቼ ዲሞክራሲ ባለበት ዓለም እንዲያድጉ ነው ፍላጎቴ” ሲል ለሮይተርስ ተናግሯል።

አዲሱ የሕግ ማሻሻያ የተመረጡ የመንግሥት ባለሥልጣናት የፍርድ ቤት ዳኛ የመምረጥ ኃይል እንዲኖራቸውና ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ጉልበት ይሰጣቸዋል።

ይህ ጉዳይ እስራኤል ውስጥ ከፍተኛ መከፋፈል ፈጥሯል። የእስራኤል ጦር ሠራዊት የጀርባ አጥንት ናቸው የሚባሉት ተጠባባቂዎች ሕጉን በመቃወም ጦሩን አናገለግልም ይላሉ የሚል ስጋት አለ።

ባለፈው ሰኞ በርካታ የእስራኤል አየር ኃይል አባላት የሆኑ ተጠባባቂ የጦር ጀት አብራሪዎች ሥልጠና አንወስድም ሲሉ አቋማቸውን ገልጠዋል።

ነገር ግን በኋላ ሥልጠናውን ለመውሰድና ከአዛዦቻቸው ጋር ምክክር ለማድረግ ተስማምተዋል።

ሐሙስ ዕለት ተቃዋሚዎች መንገድ ዘግተው ኔታኒያሁ የነበሩበትን መኪና አናንቀሳቅስም ቢሉም የኃሏ ኃሏ ኔታኒያሁ ወደ ሮም በረዋል።

መንግሥት ከፍተኛው ተቃውሞ ቢገጥመውም ጉዳዩን እያባባሱ ያሉት ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ናቸው በማለት ከአቋሜ ፍንክች አልልም ብሏል።

ተቃዋሚዎች እንደሚሉት ወደ ሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የተላከው ማሻሻያ የፍትሕ አካላትን ፖለቲካዊ በማድረግ ሃገሪቱን ወደ አምባገነናዊ ሥርዓት ይወስዳታል ይላሉ።

ኔታኒያሁ፤ ማሻሻያው ፍርድ ቤቶች ያላቸውን ረዥም እጅ ለመግታት ያለመ ሲሆን ሕጉን ሕዝቡ ባለፈው ምርጫ ያፀደቀው ነው ሲሉ ይሞግታሉ።