ቦሪስ ጆንሰን የእንቅስቃሴ ገደብ በመተላለፍ 'ድግስ' ላይ በመገኘታቸው ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተባለ

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እና የፍይናንስ ሚኒስትሩ ሪሺ ሱናክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እና የፍይናንስ ሚኒስትሩ ሪሺ ሱናክ

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እና የፍይናንስ ሚኒስትሩ ሪሺ ሱናክ የእንቅስቃሴ ገደብ ተላልፈው በመገኘታቸው ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተባለ።

ሁለቱ የዩኬ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኮቪድ-19 ወቅት ተጥሎ የነበረውን የእንቅስቃሴ እና የመሰብሰብ ክልከላን በመተላለፍ መጠጥ በሚቀርብበት መርሃ ግብር ላይ ተሳታፊ በመሆናቸው በፖሊስ ቀጣት ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ሁለቱ ግለሰቦች ከፖሊስ ማሳሰቢያ እንደደረሳቸው እና ቅጣት እንደሚጣልባቸው አረጋግጧል።

ፖሊስ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከለከል የወጡት መመሪያዎችን በመተላለፍ በዶውኒንግ ስትሪት እና ዋይትሆል ተካሂደዋል የተባሉ12 መርሃ ግብሮችን እየመረመረ ይገኛል።

ይሁን እንጂ የጽ/ቤቱ ቃል አቀባይ ፖሊስ በሁለቱ ግለሰቦች ላይ ቅጣት የሚጥልባቸው በየትኛው መርሃ ግብር በመገኘታቸው እንደሆነ አላወቅንም ብለዋል።

እስካሁን ድረስ ፖሊስ ከ50 በላይ የሆኑ ግለሰቦችን ቀጥቷል። ፖሊስ ቅጣት የምጥልባቸውን ሰዎችን ማንነት ይፋ አላደርግም ቢልም የዩኬ መንግሥት ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የፋይናንስ ሚኒስትሩ ቅጣት የሚጣልባቸው ከሆነ አሳውቃለሁ ብሎ ነበር።

የሌበር ፓርቲ መሪ ሰር ኪዬር ስታመር "ቦሪስ ጆንሰን እና ሪሺ ሱናክ ሕግ ተላልፈዋል። የብሪታኒያ ሕዝብን በተደጋጋሚ ዋሽተዋል። ሁለቱም በገዛ ፍቃዳቸው ሥራቸውን መልቀቅ አለባቸው" ብለዋል።

የሌበር ፓርቲ መሪው ጨምረውም፤ "ወግ አጥባቂ መሪዎቹ ለማስተዳደር በጭራሽ ብቁ አይደሉም። ብሪታኒያ ከዚህ የተሻለ ይገባታል" ብለዋል።