ፈረንሳይ ከዘር ጭፍጨፋ ጋር በተያያዘ ለነበራት ሚና ሩዋንዳን ይቅርታ ጠየቀች

ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአበባ ጉንጉን ሲያበረክቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ፈረንሳይ በሩዋንዳ ከ27 ዓመታት በፊት በተፈጸመው የዘር ፍጅት ለነበራት ሚና አገሪቱን ይቅርታ ተማጸነች፡፡

ፈረንሳይ ይቅርታ የጠየቀችው በፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አማካኝነት ነው፡፡

ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሩዋንዳ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

እንደ አውሮጳዊያኑ በ1994 በሩዋንዳ በተፈጸመ እጅግ አሰቃቂ የዘር ፍጅት በመቶ ቀናት ብቻ 800ሺህ ሩዋንዳዊያን ተገድለዋል፡፡

ይህን አሐዝ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚያስጠጉትም አሉ፡፡

በዚያ የዘር ፍጅት በዋናነት የተጨፈጨፉት ቱትሲዎች ቢሆኑም ለዘብተኛ ሁቱዎችም ከሞት አላመለጡም፡፡

ኪጋሊ ላይ ለዚህ የዘር ፍጅት መታሰቢያ እንዲሆን በተገነባው ዝክረ-ማዕከል ቆመው ኢማኑኤል ማክሮን ባደረጉት ንግግር ፈረንሳይ እልቂቱ እንደሚመጣ ቀድማ ማስገንዘብ ባለመቻሏ እንዲሁም እውነታው እንዲወጣ ምርመራ ማድረግ ሲገባት ለረዥም ጊዜ ዝምታን በመምረጧ ትጸጸታለች ብለዋል፡፡

ነገር ግን ፈረንሳይ በዘር ማጥፋቱ ተሳትፎ እጇ እንዳልነበረበት ማክሮን አበክረው አስገንዝበዋል፡፡

የሩዋንዳው አቻቸው ፖል ካጋሜ የማክሮንን ንግግር አወድሰው ይቅርታ መጠየቃቸው ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በመጋቢት የተሰየመው የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ፈረንሳይ በወቅቱ የሩዋንዳው የዘር ፍጅትና እልቂቱን ማስቆም እየቻለች ቸልታን መርጣ ነበር፤ ሆኖም ግን በፍጅቱ እጇ የለበትም ሲል ብያኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡

ይህ ብያኔ በዋናነት ፈረንሳይ በዚያ እልቂት ያ ሁሉ ሲሆን ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብላ እንደነበር አጋልጧል፡፡

ማክሮን በይቅርታ ተማጽኗቸው ‹ያን ምሽት በዚያ ሰቆቃ ያለፉት ብቻ ናቸው ይቅርታቸውን የምንማጸናቸው› › ሲሉ በመታሰቢያው ባደረጉት ንግግር ጸጸታቸውን አስተጋብተዋል፡፡

ኢማኑኤል ማክሮን ተገኝተው ንግግር ያደረጉበት የዘር ፍጅት ዝክረ ማዕከሉ ሩብ ሚሊዮን ሩዋንዳዊያን የተቀበሩበት ቦታ ነው፡፡

‹‹ እዚህ ለናንተ ክብር ዝቅ ብዬ ከጎናችሁ ቆሜያለሁ፤ ኃላፊነታችንን ለመወጣት ምን ያህል እንዝህላል እንደነበርን ለመረዳት በቅቻለሁ›› ብለዋል ማክሮን፣ በይቅርታ ተማጽኗቸው፡፡

በሩዋንዳ የዘር ፍጅት ዋዜማ በአገሪቱ አመራር ሥልጣን ላይ የነበሩት የሁቱ ዘር ያላቸው ልሂቃን ነበሩ፡፡

እንደ አውሮጳዊያኑ በ1994 ከመጋቢት እስከ ሰኔ በተደረገው ጦርነት ቱትሲዎች የሚመሩት አማጺ ቡድን ኪጋሊን መቆጣጠር ቻለ፡፡

የዚህ የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር(አር ፒ ኤፍ) አማጺ የያኔው የጦር አበጋዝ ፖል ካጋሜ በሁቱ የሚመራውን መንግሥት ድል ካደረጉ በኋላ ዛሬም ድረስ ሩዋንዳን እየመሩ ይገኛሉ፡፡

በዚያን ዘመን ፈረንሳይን ይመሩ የነበሩት ፍንኮስ ሚተራንድ ለሁቱ የያኔው ፕሬዝዳንት ለጁቬናል ሐቢየሪማና ቅርብ ወዳጅ ነበሩ፡፡

የሩዋንዳ የዘር ፍጅት የተጀመረው በመጋቢት 6፣ 1994 የሁቱ ዘር የነበራቸው እኚሁ ፕሬዝዳንት ጁቬኔል ሐቢያሪማና እና የቡሩንዲው አቻቸውና የሁቱ ዘር ያላቸው ሳይፕሪን ንታሪያሚራ የተሳፈሩበት አውሮፕላን አየር ላይ ሳለ ተመቶ በመጋየቱ ሁለቱም መሪዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ሁለቱ መሪዎች የተሳፈሩበት አውሮፕላን ማን አጋየው የሚለው እስከዛሬም ምላሽ አላገኘም፡፡

ፈረንሳይ በሩዋንዳ ጭፍጨፋ እጇ ይኑርበት አይኑርበት ለመበየን በወቅቱ የነበሩ መዛግብቶች ብሔራዊ ምስጢር ሆነው በመደበቃቸው ውሉ ሳይለይለት ቆይቶ ነበር፡፡

በመጨረሻም ፕሬዝዳንት ማክሮን ሰነዶቹ ለምርመራ እንዲወጡ በመፍቀዳቸው ነው እውነት አፈላላጊ ኮሚሽኑ ሪፖርት ማውጣት የቻለው፡፡