ጆ ባይደን፡ ትራምፕ "በጭራሽ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው አይደለም"

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዶናልድ ትራምፕ በጭራሽ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው አይደለም ሲሉ ተናገሩ።

በእውነቱ የሰውየውን ፍላጎትና ምን ማሳካት እንደፈለገ አይገባኝም፤ ነገር ግን በጭራሽ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው አይደለም። ለዓለም ስለ አሜሪካ ዴሞክራሲ የሚያስተላልፈው መልእክትም አሉታዊ ነው ብለዋል ባይደን።

ባይደን ይህን ያሉት ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ጊዜ ነው፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ምርጫ ተጭበርብሯል፤ ድምጽ በድጋሚ ይቆጠርልኝ ባሏቸው ግዛቶች በአንዳንዶቹ ይኸው እየሆነ ነው።

በደቡባዊ አሜሪካ ግዛት ጆርጂያ ለምሳሌ በድጋሚ በማሽን ሳይሆን በሰው ቆጠራ ተካሄዶ ጆ ባይደን በ12ሺህ 284 ድምጽ ብልጫ ማግኘታቸው ተረጋግጧል።

ባይደን እንዳሉት "ትራምፕ ከዚህ በኋላ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኖ እንደማያሸንፍ አሳምሮ ያውቃል፤ አሁን እያሳየ ያለው ባሕሪ የኃላፊነት ስሜት ማጣት ነው"።

ጆ ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው በጃንዋሪ ወር ሥልጣናቸውን ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዶናልድ ትራምፕ ግን አሁንም ቢሆን መሸነፌን አላምንም እንዳሉ አሉ።

ጆ ባይደን በብዙኃን ድምጽ ቆጠራ ተቀናቃኛቸውን ዶናልድ ትራምፕን በ5 ሚሊዮን 900ሺ የመራጭ ድምጽ ይበልጧቸዋል።

ሆኖም የብዙ አሜሪካዊያንን ድምጽ ማግኘት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ተመራጭ አያደርግም።

ባይደን 306 ኤሌክቶራል ድምጽ ሲያገኙ ትራምፕ ግን 232 ብቻ ነው ማግኘት የቻሉት።

በግዛት ተወካዮች አቆጣጠር (ኤሌክቶራል ቮት) ፕሬዝዳንት ለመሆን የሚያስፈልገው ድምጽ ደግሞ 270 እና ከዚያ በላይ ነው።

በጆርጂያ ድጋሚ ቆጠራ ወቅት 6ሺ ድምጾች እንዳልተቆጠሩ ተደርሶበታል። ይህ አሐዝ ግን ጠቅላላ ውጤቱን የሚቀይር አልሆነም። በቆጠራ ሂደት የተፈጠረ ስህተት እንጂ ትራምፕና ጠበቆቻቸው እንደሚከሱት ሆን ተብሎ የመጭበርበር ሙከራ እንዳልሆነም ተደርሶበታል።

ጆ ባይደን የሪፐብሊካንና ዲሞክራቲክ ገዥዎች በተገኙበት የበይነ መረብ ስብሰባ ላይ ተቀናቃኛቸውን እንደገለጹት "ትራምፕ ለቀሪው መጥፎ ምሳሌ እየሆነ ነው። በእውነቱ እሱ የሚያስበው ምን እንደሆነ ማወቅ ከባድ ነው፤ ነገር ግን በአሜሪካ ታሪክ ኃላፊነት የማይሰማው ሰው በመሆን በታሪክ የሚታወስ ይሆናል" ብለዋል።

ቀጥለውም፣ ትራምፕ ይሄ ሰውዬ እያደረገ ያለው ነገር በአጠቃላይ ‹‹ደም የሚያፈላ ነው›› ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡

የዶናልድ ትራምፕ ጠበቆች በጆርጂያ፣ በአሪዞና እና በፔኒሲልቬኒያ ግዛቶች ውጤቶች ውድቅ እንዲደረጉ ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበው ሁሉም አቤቱታቸው ውድቅ እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡

በሚሺጋን ግዛት ደግሞ የመጨረሻ የፍርድ ቤት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው፡፡