በዚህ ዓመት በጣና ላይ የሚታየውን አረም ለማጥፋት እየተሰራ ነው

ጣና ሐይቅ

የፎቶው ባለመብት, Kalkidan

በ2013 ዓ.ም በጣና ሐይቅ ላይ በዓይን የሚታየውን አረም ለማጥፋት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ።

ትኩረቱን እምቦጭ እና ሌሎች መጤ አረሞች ላይ ያደረገው የጣና ሃይቅና ሌሎች ውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አያሌው ወንዴ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት በዘንድሮው ዓመት በዓይን ሊታይ የሚችለውን አረም ለማስወገድ ይሰራል ብለዋል።

በዚህም በዕቅዱ መሠረት ሙሉ በሙሉ በዓይን የሚታይ አረም እንዳይኖር የሚደረግ ቢሆንም በቀጣዩ ዓመት የእምቦጩ ዘር በተለያየ ምክንያት ሐይቁ ላይ በመቅረት 10 በመቶ አረም በድጋሚ ሊኖር ይችላል ብለዋል።

በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም በአንድ ወር ዘመቻ ለማጥፋት ከጥቅምት 09 እስከ ህዳር 09/2013 ዓ.ም የሚቆይ የአንድ ወር ዘመቻ መጀመሩ ይታወቃል።

የዘመቻው ዋና ዓላማ 90 በመቶ እምቦጭን ከጣና ሐይቅ ለማረም እና ክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮችን በማቀናጀት በጋራ ችግሩን በመፍታት ተምሳሌት ለማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዘመቻው አፈጻጸም ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ ክትትል እና ግምገማ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ከሰው ሃይል በተጨማሪ በማሽን እና ትራክተር የተደገፈ ዘመቻ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀን ወደ 12ሺህ ሰው ወደ ሥራ ለማሰማራት ታቅዶ እስካሁን በቀን ከ11 ሺህ በላይ ሰዎችን ማሰማራት ተችሏል።

43 የማስወገጃ ጣቢያ ባሉት በዚህ ዘመቻ ላይ ከአንድ ወረዳ በስተቀር በሌሎች ወረዳዎች ዕቅዱን እንደሚሳካ ግምት አለ ብለዋል።

እምቦጭን ከጣና ሃይቅ ለማስወገድ የተጀመረው ዘመቻ በሁሉም ቀበሌዎች መጀመሩን ያስረዱት ዶክተር አያሌው እስካሁን ምን ያህል የሐይቁ ክፍል ከእምቦጭ እንደጸዳ ግን አልገለጹም።

ከተለያዩ አካባቢዎች ለዘመቻው የሚመጡ ሰዎች የሚቆዩ ለተወሰነ ጊዜ መሆኑ እና ከኮሮናቫይረስ ስጋት ጋር ተያይዞ ሰዎች በገንዘብ እና በቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ባልደረባ እና የብሔራዊ ደረጃ የቴክኒክ ኮሚቴ ተወካይ የሆኑት አቶ ዮሃንስ ዘሪሁን በበኩላቸው እምቦጭን ለማስወገድ ባለሃብቶች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የልማት ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ወንዞች እና የጣና ሐይቅ ከሚገናኙባቸው 15 ቦታዎች 5 የሚደርሱትን አረሙን በማስወገድ በምትኩ ደንገል እና የእንስሳት መኖ በመትከል ሐይቁ ራሱ እንዲያገግም ጭምር መታቀዱን አስታውቀዋል።

እምቦች አረም በሦስት ዞኖች፣ 9 ወረዳዎች እና አንድ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በ30 ቀበሌዎች ላይ ተንስፋፍቶ 4 ሺህ 300 ሄክታር የሚሆነው የሐይቁን ክፍልም ወሯል፡፡