በአሜሪካ ሲካሄድ የነበረ የኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራ ተቋረጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት ሲያካሂድ የነበረውን ምርምር አንድ በጎ ፍቃደኛ መታመሙን ተከትሎ ማቋረጡን አስታወቀ።
ኩባንያው እንዳለው በክትባት ሙከራው ላይ እየተሳተፈ የነበረው በጎ ፍቃደኛ የጤና እክል የገጠመው ክትባት ለማግኘት ከሚደረገው ምርምር ጋር ተያይዞ ስለመሆኑ ይጣራል።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በጎ ፍቃደኞች በሚሳተፉበት ምርምር ላይ በጎ ፍቃደኞች የጤና እክል ሊገጥማቸው እንደሚችል ኩባንያው አስታውሶ፤ ለጥንቃቄ ሲባል ሶስተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው የሙከራ ምርምሩ እንቋዲረጥ ተደርጓል ብሏል።
የበጎ ፍቃደኛውን ግላዊ መብት ለመጠበቅ ሲባል የተሳታፊው ማንነት እና ያጋጠመው ህመም እንደማይገለጽ ተጠቁሟል።
የኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራ እንዲቋረጥ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በዩናይትድ ኪንግደም በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና አስትራ ዜኔካ ጥምረት ሲካሄድ የነበረው ምርምር ላይ አንድ በጎ ፍቃደኛ ላይ የጤና መቃወስ ማጋጠሙን ተከትሎ ሙከራው ከተቋረጠ በኋላ ምርምሩ እንደገና መጀመሩ ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ከ180 በላይ የኮሮናቫይረስ ክትባት ምርምሮች እየተካሄዱ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ አንዳቸውም የክሊኒካል ሙከራቸውን ማጠናቀቅ አልቻሉም።
ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ኩባንያ እያካሄደ ያለው የኮሮናቫይረስ ምርምር ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና አስትራ ዜኔካ የደረሱበት ደረጃ ላይ መድረስ የቻለ ነበር።
ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ሲያካሂድ በነበረው የምርምር ስራ ላይ በጎ ፍቃደኞችን መመልመል የጀመረው መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።
ሙከራው 60ሺህ ተሳታፊዎችን በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ያሳትፋል ተብሎ ነበር።












