ስደት፡ ከአንድ ወር በላይ በባህር ላይ የቆዩ ስደተኞች ጣሊያን እንዲያርፉ ተፈቀደላቸው

መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Maersk Tankers/Reuters

ስደተኞቹ ሕይወታችንን እንለውጣለን ብለው ከሊቢያ የተነሱት ከአንድ ወር ከ10 ቀን ገደማ በፊት ነበር።

ታዲያ ሜዲትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ የተሳፈሩባት ጀልባ ካሰበችበት ሳትደርስ መስጠም ጀመረች።

ይህን ጊዜ ነበር የዴንማርክ የነዳጅ መርከብ 'ማእርስክ ኢቴኔ' ደርሳ ከሞት የታደገቻቸው።

የመርከብ ድርጅቱ ስደተኞቹን ካሉበት ሁኔታ እንድናወጣቸው የጠየቁን የማልታ ባለሥልጣናት ናቸው ብለዋል።

ማልታ ግን "እኔ ይህንን አላልኩም ፤ ጭራሽ ስደተኞቹንም የታደጓቸው ከእኔ የውሃ ክልል ውጭ ነው" ብላለች።

ጣሊያንም ሆነች ሊቢያ ስደተኞቹን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ስደተኞቹ በባህሩ ላይ እንዲቆዩ ተገደዋል ብላለች ማእርስክ።

መርከቧ በየትኛውም አገር እንዳያርፍ ፈቃድ ሳታገኝ በመቅረቷም፤ አንድ ነፍሰጡር ሴትን ጨምሮ 27ቱ ስደተኞች 40 ቀናትን በዚያው በባህር ላይ እንዲያሳልፉ ተገደዋል።

በመጨረሻም ስደተኞቹ ጣሊያን እንዲያርፉ ተፈቅዶላቸው፤ ቅዳሜ ዕለት ምሽት በሜዲትራኒያን ዳርቻ በምትገኘው ሲሲሊ ደሴት እንዲያርፉ ተደርገዋል ። ሲሲሊ ከጣሊያን 20 ግዛቶች አንዷ ናት።

ስደተኞቹ አርብ ዕለት ወደ ሜድትራንያን ሴቪንግ ሂዩማንስ በተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጀልባ እንዲዛወሩ ሆኖ ወደ ፖዛሎ ወደብ ተወስደዋል።

ስደተኞቹ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ገልጿል።

ይህ የሆነውም ግሪክ የሞሪያ የስደተኞች ካምፕ በእሳት መውደሙን ተከትሎ ከ12 ሺህ በላይ ስደተኞችን ለመታደግ እየጣረች ባለችበት ሰዓት ነው።

ባለፈው ሳምንት ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅትና ዓለም አቀፉ የመርከቦች ድርጅት ስደተኞቹ እንዲያርፉ ጥሪ አቅርበው ነበር።

በተመሳሳይ ባለፈው ወርም ድርጅቶቹ ባደረጉት ጥሪ 353 ስደተኞች በሲሲሊ ደሴት እንዲያርፉ መደረጋቸው ይታወሳል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ጠቅሶ በዘገበው መረጃ መሰረት በዚህ ዓመት ብቻ 19 ሺህ 400 ስደተኞች በጣሊያን ወደቦች ላይ እንዲያርፉ የተደረገ ሲሆን፤ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 5 ሺህ 200 ጋር ሲነፃፀር ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛ ነው።

በተያዘው ዓመት ከሰሜን አፍሪካ 40 ሺህ ስደተኞች ባህር አቋርጠው አውሮፓ መድረሳቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል። ከ400 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሞተዋል አሊያም የገቡበት አልታወቀም።