ሐሰተኛ የኮሮናቫይረስ ክትባት የሰጡ ኡጋንዳውያን በቁጥጥር ስር ዋሉ

ፊቷን የሸፈነች ቻእናዊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኡጋንዳ ውስጥ ሐሰተኛ የኮሮናቫይረስ ክትባት የሰጡ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአገሪቱ ፖሊስ አስታወቀ።

በኡጋንዳ እስካሁን ድረስ በኮሮናቫይረስ የተያዘ አንድም ሰው ባይኖርም አባትና ልጅ ግን መከላከያ ነው ያሉትን ክትባት መስጠታቸው ተደርሶበታል ተብሏል።

በዓለም ላይ 3800 ሰዎችን የገደለው የኮሮናቫይረስ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት መከላከያ ክትባት አልተገኘለትም።

ግለሰቦቹ ይኖሩ የነበሩት ከኡጋንዳ ዋና መዲና 120 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ማዩጌ ሲሆን ፖሊስ ከባለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ መረጃው እንደደረሰው ማወቅ ተችሏል።

አባትና ልጅ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በዋስ የተለቀቁ ሲሆን ተጨማሪ ምርመራ እንደሚደረግ ማወቅ ተችሏል።

ተጠርጣሪዎቹ ለሰዎች በአፍ የሚወሰድ ፈሳሽ ይሰጡ የነበረ ሲሆን ፖሊስ የፈሳሹን ናሙና በመውሰድ ምርመራ እያደረገ ይገኛል።

እስካሁን ድረስ ምን ያህል ሰዎች ከኮሮናቫይረስ ይከላከላል የተባለውን ሐሰተኛ ክትባት እንደወሰዱ ለማወቅ አልተቻለም።።

የኡጋንዳ ፖሊስ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግለሰቦቹ ሐሰተኛውን የኮሮናቫይረስ መድሃኒት ለሰዎች ይሰጡ የነበረው በነጻ ሲሆን በኋላ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ሲፈጠር ለማስከፈል አቅደው ነበር ተብሏል።

የኮሮናቫይረስ በዓለም ዙሪያ ባሉ ከሰማኒያ በላይ አገራት ውስጥ ተዛምቶ 100 ሺህ ያህል ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል።

በዚህም ሳቢያ ወረርሽኙ የወቅቱ የዓለም ሕዝብ ስጋት ሆኗል።