የዩናይትድ ኪንግደም ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በኮሮናቫይረስ ተያዙ

የዩኬ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣ ናዲን ዶሪስ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተሰማ።
ሚኒስትሯ በዩኬ በቫይረሱ የተያዙ የመጀመሪያዋ የሕዝብ እንደራሴ ሲሆኑ ቫይረሱ ከተገኘባቸው በኋላ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ አንደወሰዱና ራሳቸውንም ከሌሎች አግልለው መቀመጣቸውን ተናግረዋል።
በዩኬ እስካሁን ድረስ በቫይረሱ ተይዘው የነበሩ ስድስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን 382 ደግሞ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተሰምቷል።
በቅርቡ በቫይረሱ ከተያዙና ከሞቱ ግለሰቦች መካከል የ80 ዓመት አዛውንት የሚገኙበት ሲሆን ግለሰቡ ሌሎች የጤና ችግሮች ነበሩባቸው ተብሏል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ፣ ናዲን ዶሪስ ያገኟቸው ሰዎች በአጠቃላይ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑ ታውቋል።
ሚኒስትሯ የቫይረሱን ምልክት ማሳየት የጀመሩት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት እንደነበር የተነገረ ሲሆን በዚያው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ባዘጋጁት ስነስርዓት ላይ ተሳትፈው ነበር።
ከአርብ ዕለት ጀምሮም ግን ራሳቸውን ከሰው አግልለው መቀመጣቸው ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ያድርጉ አያድርጉ የታወቀ ነገር የለም። ከሚኒስትሯ ጋር ግንኙነት የነበራቸው የጤና ሚኒስትር መስሪያቤቱ ከፍተኛ አመራሮች በአጠቃላይ ምርመራ እንደተደረገላቸው እንዳለ ተነግሯል።















