ወደ እስራኤል የሚገቡ መንገደኞች በሙሉ ለ14 ቀን ራሳቸውን ለይተው እንዲያቆዩ ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ማንኛውም ወደ እስራኤል የሚያቀና መንገደኛ ለ14 ቀን ራሱን ለይቶ እንዲያቆይ መወሰኑ ተሰምቷል።
ይህ ውሳኔ የመጣው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚል ሲሆን ውሳኔውንም የተናገሩት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ናቸው።
"ከተለያዩ አገራት ወደ እስራኤል የሚመጡ ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ይቀመጣሉ" ብለዋል በትዊተራቸው ላይ ባሰፈሩት የተንቀሳቃሽ ምስል መልዕክት።
የእስራኤል የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር አርያ ዴሪ እርምጃው ከተለያዩ አገራት የሚመጡ እስራኤላውያን ላይም ወዲያውኑ ተፈፃሚ እንደሚሆን ገልፀዋል።
ለውጪ አገራት ዜጎች ግን ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ሲሉ አስታውቀዋል።
ይህ እርምጃ ተግባራዊ ሲሆን ከውጪ አገራት የሚመጡ የሌላ አገር ዜጎች ተነጥለው ሊያርፉ የሚችሉበት ቦታ እንዳላቸው ማረጋገጥ መቻል አለባቸው ማለት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ " ከረዥም ክርክር በኋላ ውሳኔውን አስተላልፈናል። ማንኛውም ወደ እስራኤል የሚመጣ ሰው ለ14 ቀን ተለይቶ መቆየት አለበት" ብለዋል በመግለጫቸው ላይ።
"ይህ ውሳኔ አስቸጋሪ ውሳኔ ነው። ነገር ግን የሕዝብ ጤናን ለመጠበቅ ማኝኛውንም ነገር ማድረግ አለብን" በማለት ውሳኔው ለሁለት ሳምንት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ውሳኔው ተግባራዊ ሲሆን በባህር ማዶ የሚገኙ 268 ሺህ እስራኤላውያን ወደ አገራቸው ሲመለሱ ራሳቸውን ከሰው አግልለው ማቆየት ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው።
9 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት እስራኤል እስካሁን 42 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን የሞተ ግን የለም።
እስራኤል ከተለያየ አገራት የሚገቡ መንገደኞች ላይ እገዳ የጣለች ሲሆን ከእነዚህም መካከል ጣሊያን አንዷ ናት።
እስካሁን ድረስ በዓለም ላይ 111 ሺህ ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን 3890 ሞት ተመዝግቧል።













