በሆንግ ኮንግ ዩኒቨርስቲ 4,000 ተቀጣጣይ ነገሮች መገኘታቸውን ፖሊስ ገለጸ

የሆንግ ኮንግ ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሆንግ ኮንግ ፖሊስ፤ በፖሊ ቴክኒክ ዩኒቨርስቲ ጊቢ ውስጥ 4,000 ተቀጣጣይ ጋዝ ጠርሙስ ውስጥ በመጨመር የተሠሩ ቦንቦች (ፔትሮል ቦንብ) ማግኘቱን ገለጸ።

ፖሊሶች ለሁለት ቀናት ዩኒቨርስቲውን ሲያጸዱ ነበር ተቀጣጣዮቹን ያገኙት።

በዩኒቨርስቲው በመብት ተሟጋቾች እና በፖሊስ መካከል ፍጥጫ ነበር። ፖሊሶች ወደ ዩኒቨርስቲው የገቡት ተቃዋሚዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ነበር።

3,989 ተቀጣጣይ ጋዝ ጠርሙስ ውስጥ በመጨመር የተሠሩ ቦንቦች እና 573 መሣሪያም በዩኒቨርስቲው ተገኝቷል። ተቃዋሚዎች ለሁለት ሳምንት በዩኒቨርስቲው መሽገው የነበረ ሲሆን፤ አሁን ዩኒቨርስቲው በአስተዳዳሪዎቹ ሥር ተመልሷል።

ተቃዋሚዎች ፖሊስ ላይ ድንጋይ፣ ቀስትና ሌሎችም መሣሪያዎች ተጠቅመው ነበር። 1,377 ሰዎች በቁጥጥር ሥርም ውለዋል።

በፖሊ ቴክኒክ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ለቀናት ከታገቱ መካከል የ19 ዓመቱ ተማሪ ኤልቪስ ይገኝበታል። "ብዙ ሰዎች ተይዘው ነበር፤ ሦስት ጊዜ ለማምለጥ ሞክረን ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስ ስለተኮሱብን አልተሳካልንም፤ በጣም አስፈሪ ነበር፤ ደም በየቦታው ይታይም ነበር" ብሏል።

ጋዜጠኞችና ሀኪሞች ባቀረቡት ቁሳ ቁስ በመጠቀም ተቃዋሚዎች ምግብ እያበሰሉ ነበር።

"ውሀው የአስለቃሽ ጭስ ጣዕም ነበረው፤ እስከ አራት ቀን የታሸገ ውሀ እስኪያልቅ ጠጥተናል" ሲልም ሁኔታውን ገልጿል።

አንዳንድ ተቃዋሚዎች በገመድ ተንጠላጥለው ከዩኒቨርስቲው ቢያመልጡም፤ ኤልቪስ ስጋት ስለገባውና ሰዎችን ጥሎ ማምለጥ ስላልተዋጠለት ይህንን አማራጭ አልተጠቀመም። አንድ ጊዜ ለማምለጥ ቢሞክርም እግሩ ላይ ጉዳት ደርሶበታል።

በአምስተኛው ቀን የግል መረጃው ተመዝግቦ ወደ ሆስፒታል እንዲሄድ ተደርጓል።