የግብፅ አፈ ጉባኤ የሂትለርን መሰረተ ልማት ግንባታ አንቆለጳጰሱ

የግብፅ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አሊ አብደል አል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የግብፅ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አሊ አብደል አል ንግግሬ "ከማዕቀፉ ውጪ" ተወስዶብኛል ሲሉ ተናግረዋል

የግብፅ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የሆኑት የናዚን አምባገነን አዶልፍ ሂትለርን መሰረተ ልማት ፕሮጀክት ማንቆለጳጰሳቸው በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ተጠቃሚዎች ዘንድ ቁጣን ቀሰቀሰ።

አሊ አብደል አል ይህንን አስተያየት የሰጡት የግብፁ ፕሬዝዳንት የአብዱል ፈታህ አልሲሲን የዕድገት ዕቅዶች ደግፈው ንግግር ሲያደርጉ ነው።

"ሒትለር ስህተቶች ሰርቷል። ነገር ግን ወደ ምስራቅም ሆነ ወደ ምዕራብ እንዲስፋፋ ያገዘው ጠንካራ መሰረተ ልማት መገንባት በመቻሉ ነው" ብለዋል አፈ ጉባዔው።

አፈ ጉባዔው ንግግራቸው ከማዕቀፉ ውጪ እንደተወሰደባቸው ተናግረዋል።

በግብፅ መንግሥትና ወታደሩ ከግንባታ ዘርፉ ጋር በተያያዘ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀዋል በሚል በመቶዎች የሚቆጠሩ አደባባይ በመውጣታቸው ብቻ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ግብፅ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የምጣኔ ኃብቷ የተጎዳ ሲሆን ከ30 በመቶ በላይ ዜጎቿም በድህነት የሚኖርባት ሀገር ነች።

አፈ ጉባዔው የሕዝብ እንደራሴዎችን ፕሬዝዳንቱ "ዘመናዊ የሆነች ግብፅ" ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት ለማጤን የጥሞና ጊዜ እንዲወስዱ መጠየቃቸውን 'ሚድል ኢስት አይ' የተባለ ድረ ገፅ ዘግቧል።

በዚህ ንግግራቸው ላይ ነው "ጀርመን የገነባችው መሰረተ ልማት ለተቀረው ዓለም አርአያ የሚሆን ነው" ሲሉ የተናገሩት።

"በሽግግር ወቅት ሀገር ለመገንባት ጨከን ያለ ርምጃ መውሰድን ይጠይቃል... ምክንያቱም በዚህ ጊዜ ነው ተቋማት የሚገነቡት፣ መሰረተ ልማቶች የሚጣሉት " ሲሉ ተደምጠዋል።

ይህ አስተያየት በመንግሥት ደጋፊ መገናኛ ብዙኀን ላይ ተዘግቧል።

አዶልፍ ሂትለር ናዚ ጀርመንን በመራበት ወቅት 11 ሚሊየን ሰዎችን የጨፈጨፈ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ስድስት ሚሊየኖቹ አይሁድ በመሆናቸው ብቻ የተገደሉ ናቸው።

የአል ሲሲ ተቃዋሚዎች ወዲያውኑ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ በመውጣት ፕሬዝዳንቱን ከሂትለር ጋር ማነፃፀር ግብፅን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሳጣታል ሲሉ ኮንነዋል።

አፈ ጉባኤው ለ'ኢጅብት ቱዴይ' ሂትለር "የሰራው ወንጀል በምንም ዓይነት ሁኔታ ሊንቆለጳጰስ የማይችል ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

አክለውም "የትኛውም ሀገር ያለ ጠንካራ መሰረተ ልማት ሊያድግ አይችልም። በንግግሬ ውስጥ መጥቀስ የፈለግኩት ይህንን ብቻ ነው" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት አልሲሲ የርዕሰ ብሔርነቱን መንበር ከተረከቡ ወዲህ በግብፅ ተቃውሞዎች እንዳይካሄዱ የማፈን ሰፊ እንቅስቃሴ አለ።