ግብፅ መንግሥትን ተሳደበ ያለችውን ፀሃፊ ከሰሰች

አላ አል አስዋኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታዋቂው ግብጻው ፀሃፊ አላ አል አስዋኒ የሃገሪቱን ፕሬዝዳንቱ፣ የጦር ሠራዊቱንና የፍትህ ሥርዓቱን ተሳድበሃል በሚል በወታደራዊ አቃቢ ህግ ተከስኩ አለ።

በአሜሪካ ኑሮውን ያደረገው አስዋኒ ክሱ ከመጨረሻ መፅሃፉ 'ዘ ሪፐብሊክ፡ አስ ኢፍ' እና ለዶቼ ቬሌ በአረበኛ ከፃፋቸው ፅሁፎች ጋር ተያያዥነት አለው ብሏል።

ክሱን የግብፅን ሕገ መንግሥት "በግልጽ የሻረ" ነው በማለት አውግዞታል።

የአስዋኒ ታዋቂው 'ዘ ያኮቢያን ቢዩልዲንግ' የተሰኘው መፅሃፍ ከአንድ ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ በ35 ቋንቋዎች ተሽጧል። መፅሃፉ ካይሮ የሚገኝ ጥንታዊ ህንፃን ተጠቅሞ በጊዜው በነበሩት የፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ አስተዳደር ስር ያለችው ግብፅ ውስጥ ተስፋፍቶ ያለውን ሙስና እና የማህበረሰብ ችግር ያሳያል።

'ዘ ሪፐብሊክ አስ ኢፍ' የተሰኘው መፅሃፍ ባለፈው ዓመት የታተመ ሲሆን እ.አ.አ በ2011 ፕሬዝዳንት ሙባረክ ስልጣን እንዲለቁ ያስገድደውን የህዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ላይ ያጠነጥናል።

የግብፅን የመንግሥት ተቋማትን፣ ምክር ቤቱን፣ ሥገ-መንግሥቱን እና ፍርድ ቤቶቹን የሚተቸው ይህ መፅሃፉ በግብፅ እንዳይሸጥም ተከልክሏል።

ባሳለፈው ሳምንት ማክሰኞ ለዶቼ ቬሌ በፃፈው ፅሁፍም ላይ አስዋኒ "በወታደራዊ ፍርድ ቤት መንግሥትን በመስደብ እና በመንግሥት ላይ ጥላቻን በማነሳሳት በሚል መከሰሴን አውቄአለው።

አስዋኒ "ብቸኛው የፈፀምኩት ወንጀል ቢኖር ፀሃፊ መሆኔ፣ ሃሳቤን በነፃነት መግለፄና [ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ] ሲሲም ቢሆኑ መተቸት በሚገባቸው በመተቸቴ ነው" ብሏል።

ይህን የተናገረው እ.አ.አ በ2013 በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠውን የሙባረክን ተከታይ መንግሥት በወታደራዊ ኃይል ከስልጣን ያባረሩትን ከፍተኛ ወታደራዊ መሪን ጠቅሶ ነው።

'ዘ ኢጂፕት ቱደይ' የተሰኘ ጋዜጣ አስዋኒ በዋናነት የተከሰሰው መጋቢት 4 ዶቼ ቬሌ ላይ በፃፈው የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሲ በዋና መሠረተ ልማቶችና በሲቪል ሠራተኛ ቦታ ወታደሮችን መሾማቸውን በሚተቸው ፅሁፉ ነው ብሏል።

አስዎኒ የተመሰረተበት ክስ የግብፅን ሕገ መንግሥት "ሃሳብንና የግል አስተያየትን የመግለፅ መብት የተጠበቀ ነው የሚለውን" አንቀፅ 65 እና ግብፅ የተስማማችበትን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብትን የሚደነግገውን አንቀፅ 19 የጣሰ ነው።

ፀሃፊው በተጨማሪም ለ"አደገኛ" የስም ማጥፋት ተጋልጫለው ብሎ፤ በዚህም በካይሮ አየር መንገድ ምንጊዜም ስሄድ እጉላላለሁ ብሏል።

አስዋኒ "ወንጀሌ ሃሳቤን በነፃነት መግለፅ ከሆነ በሃሳቦቼ ኩራት ይሰማኛል" ብሏል።

ብዙ የግብፅ አክቲቪስቶች ለአስዋኒ ድጋፋቸውን ያሳዩ ሲሆን የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆነው ጀማል ኢድ "አስዋኒን አከብረዋለው፤ ያደረገው ነገር ወንጀል ከሆነ ይህን የማድረግ መብቱን እደግፋለው" ብሎ ፅፏል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች እንደሚሉት ፕሬዝዳንት አልሲሲ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እስከ 60ሺህ የሚደርሱ ተቃዋሚዎችን አስረዋል።

በሌላ ዜና ማክሰኞ ዕለት የግብፅ መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ምክር ቤት በማህበራዊ ድረገፅ ላይ የሚገኙ ከ5ሺህ በላይ ተከታይ ያላቸው የተሳሳተ መረጃና ሰዎች ህግ እንዲተላለፉ የሚያነሳሱ አካውንቶችን እንዲዘጋ ስልጣን ተሰጥቶታል።

አካውንቶችን እንዲከታተል የተደረገው አካልም የማህበራዊ ድረገፅ ባለቤቶቹን እስከ 14 500 የአሜሪካ ዶላር የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይጠብቅ መቅጣት ይችላል።