አንሶላችንን መቀየር ያለብን በምን ያህል ቀናት ልዩነት መሆን አለበት?

አንሶላ ሲቀየር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ነገሩ በአደባባይ አይወራም የሚሉ ብዙ ናቸው። ግን የአንሶላ ቅያሪ ጉዳይ የሁላችንንም ደጅ ያንኳኳል።

ብዙዎች በምን ያህል ቀናት አንሶላ ይቀየር? በሚለው ቁጥር ላይ አይስማሙም። እርስዎ ግን በምን ያክል ጊዜ አንሶላዎ ይቀይራሉ/ ያጥባሉ?

አንሶላ በምን ያህል ቀናት ልዩነት መቀየር አለበት የሚለውን ከጤና ጋር የሚያስተሳስሩ አሉ።

ስለጉዳዩ ጥናት የሠራችው ዩናይትድ ኪንግደምን እንደ ማሳያ እንውሰድ።

አንሶላ በየስንት ቀኑ ይቀየር ለሚለው ጥያቄ የተሰጠው መልስ በጥናቱ በተሳተፉ 2 ሺህ 250 ዜጎች መካከል የአቋም ልዩነት እንዳለ ጠቁሟል።

ግማሽ ያህሉ ወንደላጤዎች አንሶላቸውን ለአራት ወር እንዳላጠቡ ተናግረዋል።

12 በመቶው ደግሞ አንሶላ የሚያጥቡት ትዝ ሲላቸው ነው። ይህም ከአራት ወራት ሊበልጥ ይችላል።

የሥነ ልቦና ባለሙያ፣ ኒውሮሳይንቲስትና የእንቅልፍ ተመራማሪዋ ዶ/ር ሊንዚ ብሮውኒንግ "ይሄ ትክክል አይለም" ትላለች።

ከሴተላጤዎች 62 በመቶዎቹ በየሁለት ሳምንቱ አንሶላ እንደሚቀይሩ ይናገራሉ። የተወሰኑት ደግሞ በየሦስት ሳምንቱ።

አንሶላ መቀየር ምን ይጠቅማል?

አንሶላ በየሳምንቱ ወይም በየሁለት ሳምንቱ መቀየር አለበት ትላለች ዶ/ር ሊንዚ።

ይህ የሚደረገው ለንጽህና ሲባል ነው። ከሰውነታችን የሚወጣውን ላብ የሚሰበስበው አንሶላችን እንደመሆኑ በላብ ተጠቅልሎ መተኛት ያስቸግራል።

"ላብ አንሶላን ያሸታል፣ ይጨመድደዋለም" ትላለች ዶክተሯ።

ስንተኛ ምቾት እንዲሰማን በአካባቢያችን ነፋሻማ አየር ቢኖር ይመረጣል።

አንሶላ አለመቀየር የሚያስከትለው በላብ ተዘፍቆ መተኛትን ብቻ አይደለም። ከሰውነታችን ላይ የሚነሱ ሙት ህዋሳት እንቅልፋችንን እንዲያስተጓጉሉትም ያደርጋል።

ስንተኛ ከቆዳችን ላይ ሙት ህዋሳት ይወድቃሉ። ይህም አንሶላችን ላይ ይሰበሰባል። አንሶላ በቀናት ልዩነት የማንቀይር ከሆነ እነዚህን ሙት ህዋሳት አናስወግድም ማለት ነው።

"አንሶላችንን ቶሎ ቶሎ የማናጥብ ከሆነ ሙት ህዋሳት አንሶላው ላይ ይከማቻሉ" ትላለች ዶክተር ሊንዚ።

ችግሩ በዚህ ብቻ አያከትምም።

ማይት የሚባሉ ጥቃቅን ነፍሳት ህዋሳቱን ለመመገብ አንሶላችን ላይ ይሰበሰባሉ። ይህም ለቆዳ በሽታ ያጋልጣል። በእንቅልፍ ወቅት ምቾትም ይነሳል።

አንሶላ በምን ያህል ጊዜ ይቀየር?

ዶክተሯ እንደምትለው፣ አንሶላ ከተቻለ መቀየር ያለበት በየሳምንቱ ነው። ግን በቀዝቃዛ ወቅት ከሳምንት ጥቂት አለፍ ሊልም ይችላል።

ከሁለት ሳምንት በላይ አንሶላ ሳይቀይሩ መቆየት ግን አስጊ እንደሆነ ታስጠነቅቃለች።

ስንተኛ እጃችን በመጠኑም ቆሽሾ እንደመሆኑ አንሶላ ማቆሸሻችን አይቀርም። ከትንፋሻችን የሚመወጣውም አየር ሁሌ ንጹህ አይደለም።

አንዳንዶች ከመተኛት በፊት ሰውነት መታጠብ አንሶላ እንዳይቆሽሽ ይረዳል ቢሉም ሁነኛው መፍትሄ አንሶላ መቀየር እንደሆነ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ቶሎ አንሶላ የማንቀይረው ለምንድን ነው?

መልሱ እንደየሰዉ ይለያያል።

መግቢያችን ላይ የጠቀስነው የዩናይትድ ኪንግደም ጥናት እንደሚለው ግን፣ 67 በመቶ የአገሪቱ ዜጎች አንሶላ ቶሎ ቶሎ የማይቀይሩት ስለሚረሱት ነው።

35 በመቶው ግድ አይሰጣቸውም። 22 በመቶው ንጹህ ተለዋጭ አንሶላ አያገኙም። 38 በመቶ ያህሉ ደግሞ አንሶላ በየጊዜው መታጠብ አለበት ብለው አያስቡም።

ዶ/ር ሊንዚ፣ መኝታ ቤት እንደተቀደሰ ስፍራ ሊጠበቅ ይገባል ትላለች።

"መኝታ ቤት የምንወደው ቦታ መሆን አለበት። ወደ መኝታ ቤት ስንገባ በደስታ ልንሞላም ይገባል።"

እንቅልፍ የማጣት ችግር ያለባቸው ታካሚዎቿን ከምትመክራቸው ነገሮች መካከል አንሶላችሁን አጽዱ የሚለው አንዱ ነው።

"ንጹህ አንሶላ አንጥፈን ስንተኛ ምቾት ይሰማናል። ደስ ይለናል። እንረጋጋለን።"