እንቅልፍ ማጣት እንቅልፍ የነሳት ደቡብ ኮሪያ

ደቡብ ኮሪያዊ ጎልማሳ ተኝተው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በምድራችን ላይ እንቅልፍ ከራቃቸው ሕዝቦች መካከል ደቡብ ኮሪያውያንን የሚስተካከል የለም

ደቡብ ኮሪያ እንቅልፍ አልባ ናት። ዓለም ላይ ዞር ዞር ቢሉ በእንቅልፍ ከሚሰቃዩ ሃገራት ይመድቧታል።

ይህም በሕዝቧ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። ጂ-ኢዩን የመተኛት ችግር የጀመራት የሥራ ሰዓቷ በጣም አስጨናቂ ከሆነባት በኋላ ነበር።

በኋላም መዝናናት እስካለመቻል ደረሰች።በብዛትም ከጠዋት 1:00 ሰዓት እስከ ምሽት 4:00 ሰዓት ሥራዋ ላይ ታሳልፋለች።

ይህ አማካይ የሚባለው ነው። ሥራ ሲበዛስ? የ29 ዓመቷ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሥራ ሲበዛ እስከ ምሽት 9፡00 ሰዓት በቢሮዋ ስትሯሯጥ ራሷን ታገኘዋለች።ብዙ ጊዜም አለቃዋ እኩለ ሌሊት ላይ ይደውላል። 'ሥራ አለቀ ወይ?' ለማለት አይደለም። የሚደውለው በፍጥነት መጠናቀቅ ስላለበት ሥራ ትዕዛዝ ለመስጠት ነው።

"እንዴት መዝናናት እንዳለብኝ የረሳሁ ያህል ይሰማኛል" ትላለች።በሴኡል የሚገኘው ጋንግናም የተባለው መንደር ድምቅ ድምቅምቅ ያለ ነው።

መቀመጫውን በዚሁ መንደር ያደረገ ድሪም ስሊፕ የተሰኘ ክሊኒክ ይገኛል። ዶክተር ጂ-ሂዮን ሊ ደግሞ በክሊኒኩ የእንቅልፍ የሥነ አእምሮ ሐኪም ናቸው።

በቀን እስከ 20 የእንቅልፍ ኪኒኖች የሚወስዱ ደንበኞች ቁጥር የትለሌ ነው ይላሉ።

"ብዙውን ጊዜ ለመተኛት ጊዜ ያስፈልጋል። ኮሪያውያን ግን ጀርባቸው አልጋ እንደነካ መተኛት ይፈልጋሉ። ለዚህም ነው ኪኒን የሚወስዱት" ይላሉ።

የእንቅልፍ መድሃኒት ሱስ ብሔራዊ ወረርሽኝ ለመሆን በቅቷል። 100,000 ኮሪያውያን የእንቅልፍ ክኒን ሱስ እንደያዛቸው ይገመታል። አሃዙ ኦፊሴሊያዊ መረጃ ግን አይደለም።

ኪኒን ወስደውም እንቅልፍ የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው። መፍትሔ ያሉት ደግሞ ኪኒኑ ላይ አልኮል መደረብ ነው።

ከድጡ ወደ ማጡ እንደማለት ነው። ''አንዳንዶች ተኝተውም ይንቀሳቀሳሉ። ወደ ማቀዝቀዣው ሄደው ብዙ ነገር ይበላሉ። አንዳንዴም ያልበሰለ ምግብን ጭምር ይበላሉ።

ይህ ሁሉ ሲሆን ምንም አያውቁም። በእንቅልፍ ልባቸው መኪና የሚነዱትንም ቤቱ ይቁጠረው። ሴኡል በእንቅልፍ ልባቸው በሚያሽከረክሩ ሰዎች በርካታ የመኪና አደጋዎችም አስተናግዳለች" ይላሉ ዶክተር ሊ።

ዶ/ ር ሊ ሃይፖ-አራውሳል (ከመጠን ያለፈ ንቃት እንደማለት ነው) ተብሎ በሚታወቀው ችግር የሚሰቃዩ ሰዎችን እያዩ ነው።

በዚህም ሥር የሰደደ እንቅልፍ የማጣት ችግር የገጠማቸው ሰዎችን እያሻቀበ ነው። አንዳንድ ታካሚዎቻቸው ምሽት ላይ ለጥቂት ሰዓታት ከተኙ አሥርተ ዓመታት እንዳለፋቸው በተደጋጋሚ ነግረዋቸዋል።"ያለቅሳሉ።

እዚህ ሲመጡ የመጨረሻ ተስፋቸውን ሰንቀው ነው። ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ነው" ይላሉ።በሥራ የናወዙ፣ ውጥረት የተጫናቸው እና እንቅልፍ ማጣት ያደከማቸው ዓለምን ዞረው በእንቅልፍ እጦት የሚሰቃዩ ሃገራትን ይዘርዝሩ ቢባሉ ደቡብ ኮሪያ አንዷ ትሆናለች። በብዙ ዘርፎችም ቀዳሚ ናት።

የድሪም ስሊፕ ክሊኒክ ውስጥ የቆመች የሕክምና ባለሙያ

ካደጉት ሃገራት ተርታ ራስን በማጥፋት ረገድ ከፍተኛ ቁጥር ታስመዘግባለች።

ጠንካራ አልኮል በመጠጣትም ከቀዳሚዎቹ ተርታ ናቸው። በጣም ብዙ ሰዎች በፀረ-ጭንቀት መድሐኒቶች ታግዘው ህይወታቸውን ይገፋሉ።ለእነዚህ ስታቲስቲክስ መረጃዎች ታሪካዊ ምክንያቶችም አሉ።ሃገሪቱ እጅግ ድሃ ከሚባሉት ሃገራት ተመንድጋ በዓለም በቴክኖሎጂ ከላቁ ሃገራት ተርታ ተሰልፋለች። ይህ ደግሞ የሆነው በጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ ነው።

በፍጥነት እያደገ ባለው የፖፕ ባሕሏ ላይ ያላት ተጽእኖም ለስላሳ የሚባል ነው።ተመሳሳይ ዑደት ውስጥ የገቡ ሌሎች ሃገራትም አሉ። እንደ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ያሉ ሃገራት የተፈጥሮ ሃብታቸውን መጠቀም ይችላሉ።

ኮሪያ እንደዚህ ዓይነት እምቅ ሃብት የላትም። ለማደግ ሥራ ነው ብቸኛው መንገድ። ህዝቡ በትጋት ላቡን ጠብ አድርጎ ቁርጠኛ ሆኖ በመሥራቱ ራሱን ለውጧል።ይህ ደግሞ ብዙ ውጤት አስከትሏል።

አንደኛው ህዝቧ ከመጠን በላይ በሥራ እንዲያሳልፍ፣ እንዲጨነቅ እና እንቅልፍ እንዲያጣ አድርጓል።ይህም እንቅልፍ ላጡ መፍትሔ የሚፈልግ ኢንዱስትሪ እስኪፍጠር ደርሷል።

ኢንዱስትሪው በጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ብቻ 2.5 ቢሊዮን ዶላር እንደደረሰ ይገመታል።እያደገ ያለው የእንቅልፍ ኢንዱስትሪሴኡል ከእንቅልፍ ጋር በተያያዘ ብዙ የተለየ ነገር አላት። መደብር ሙሉ የመኝታ ቤት ቁሳቁሶችን ያገኛሉ። ከምርጥ አንሶላ እስከ ተመረጠ ትራስ ድረስ ይሸጣሉ።

ፋርማሲዎች መደርደሪያ ሙሉ ከእፅዋት የተሠሩ የእንቅልፍ መድሃኒቶች ይቸበችባሉ። ቴክኖሎጂም ኢንሶምኒያን (እንቅልፍ ማጣት ችግር) የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት ስለሆነ ጉዳይ እናጫውቶት። ዳንኤል ቱዶር የተጨነቁ ወጣት ኮሪያውያንን ለመርዳት አንድ መተግበሪያ ያስተዋውቃል። ሞኪር የተሰኘው መተግበሪያ ለሜዲቴሽን የሚጠቅም ነው።ኮሪያ በታሪክ የቡድሂስት ሃገር ናት። ወጣቶች ግን ሜዲቴሽን የአዛውንቶች ነው ይላሉ። ይባስ ብለውም በሴኡል ቢሮዎች ውስጥ የማይሞከር ሲሉ ያስባሉ።

ወጣት ኮሪያውያንን ቀልብ ለመሳብ ዳንኤል ሜዲቴሽንን የምዕራባዊያን በማስመሰል ማቅረቡን ይገልጻል።በርካታ ባህላዊ ተቋማትም በዚህ ተሳታፊ ሆነዋል።ሄይራንግ ሱኒም የቡድሃ መነኩሴ ናቸው። በሴኡል መውጫ ላይ እንቅልፍ ላጡ እና የቡድሂስትን ትምህርቶች የሚሰጥ ቤተ-መቅደስ ይመራሉ።ቀደም ባሉት ጊዜያት እንደዚህ ዓይነት እረፍቶች ትምህርት እና ጸሎት ለሚፈልጉ ጡረተኞች ብቻ ይደረግ ነበር።

አሁን አሁን ደግሞ ተሳታፊዎቹ ወጣት በሥራ ያሉ ኮሪያውያን እየሆኑ ነው። እነዚህ የቡድሃ ቤተ-መቅደሶች ለትርፍ እየሠሩ ነው ተብለው ይተቻሉ። ሄይራንግ ሱኒም "በእርግጥም ስጋቶች አሉ… ከስጋቶቹ ግን ጥቅሙ የሚበልጠ ይመስለኛል" ይላሉ።"

በባህላዊ መንገድ ካየነው ወጣቶች የቡድሃ ትምህርቶችን ፈልገው ሲመጡ ማየት ብርቅ ነበር። እናም ከቤተመቅደስ ቆይታቸው በርካታ ነገር እያገኙ ነው'' ብለዋል።

የመሠረታዊ ለውጥ አስፈላጊነትሊ ሃይ-ሪ በሥራ ላይ የሚደርስባት ጫና በመብዛቱ ከእነዚህ የቡድሃ ቤተ-መቅደሶች ወደ አንዱ አቅንታ ነበር። በኋላም ለጭንቀትዋ ኃላፊነት መውሰድን እንደተማረች ተናግራለች።"ሁሉም ነገር ከእኔ ይጀምራል። ሁሉም ችግሮች ከእኔ ይጀምራሉ። የተማርኩት ይህንኑ ነው።

''ነገር ግን ለጭንቀት እና ለእንቅልፍ እጦት የሚሆን መፍትሔ በግለሰብ ደረጃ ማቅረብ ችግር ሊሆን ይችላል።ችግሩ የተፈጠረው ምክንያታዊነት ከጎደለው የሥራ ባህል እና ከህብረተሰብ ጫና ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖች ግለሰባዊውን አካሄድ ተጎጂን ከመወንጀል እኩል ነው ሲሉ ይተቻሉ።

በቡድሂስት ቤተ መቅደስ ውስጥ ወንዶች እና ሴቶች እግራቸውን አጣምረው ተቀምጠው

እነዚህ ተቺዎች ሜዲቴሽንን ወይም መዝናናትን እንደጊዜያዊ ጥገና ያዩታል።

እውነተኛ መፍትሄዎች ሊመጡ የሚችሉት በህብረተሰቡ ላይ መሠረታዊ ለውጦች ሲደረጉ ብቻ ነው ይላሉ።ጂ-ኢዩን እንቅልፍ አጥታ እና ተጨንቃ ስለነበር ሥራዋን ውላ አድራ አቆመች። አሁን በጊዜያዊነት ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ ትሠራለች።

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያትም ከቤት መሥራት ትችላለች ማለት ነው። የእንቅልፍ እጦቷን ለመቆጣጠርም ከዶክተር ሊ ክሊኒክ የባለሙያ እርዳታ እያገኘች ነው።ጂ-ኢዩን አክላም "እንደ ሃገር የምናደርገው ጠንክሮ መሥራት አሁን ምን ዋጋ አለው? ዘና ማለት መቻል አለብን" ትላለች።