በኒውዮርክ ባቡር ጣቢያ ከ20 በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል የተባለው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካዋ ኒውዮርክ ባቡር ጣቢያ በአጠቃላይ ከ20 በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል የተባለው ተጠርጣሪ በቁጥጥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
ፖሊስ እንዳለው ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ግንኙነት እንዳለው የተጠረጠረው ፍራንክ ጄምስ የተባለው የ62 ዓመት ግለሰብ ነው በቁጥጥር ስር የዋለው።
በወቅቱ ፍራንክ ጄምስ የግንባታ ሰራተኞች እራሳቸውን ከአደጋ ለመከላከል የሚለብሱትን አድርጎ የነበረ ሲሆን እንዲሁም የጋዝ መከላከያም ፊቱ አድርጎ ነበር። በባቡር ጣቢያውም የጭስ ፈንጂዎችን ከወረወረ በኋላ ተኩስ ከፍቷል ብሏል ፖሊስ።
ይህንን ጥቃት ተከትሎ የኒው ዮርክ ፖሊስና ሌሎች የደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤቶች ባደረጉት 30 ሰአታት የፈጀ አሰሳ ነው ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ማዋል የቻሉት።
ተጠርጣሪው ፍራንክ ጄምስ ረቡዕ ከሰአት አካባቢ በቁጥጥር ስር የዋለው ማንሀተን ውስጥ ፖሊስ ጥቆማ ከደረሰው በኋላ ነው።
''ውድ የኒው ዮርክ ነዋሪዎች፤ ይዘነዋል'' ብለዋል ከንቲባው ኤሪክ አዳምስ።
ኃላፊዎች እንደገለጹት ፍራንክ ጄምስ በባቡር ጣቢያው ለደረሰው ጥቃት ብቸኛው ተጠርጣሪ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን በጥቃቱም 23 ሰዎች በአጠቃላይ ጉዳት ሲደርስባቸው 10 ሰዎች ደግሞ በተኩስ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የኒው ዮርክ ፖሊስ ኮሚሽነሩ ኪቻንት ሴዌል በበኩላቸው ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር የዋለው ያለ ምንም ችግር መሆኑን ገልጸዋል። '' ከጥቃቱ በኋላ መሸሸጊያ አጥቶ ነበር። የትም መሄጃ አልነበረውም'' ብለዋል ኮሚሽነር ኪቻንት ሴዌል።
ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር እንዲውል ማን ለፖሊስ ጥቆማ እንደሰጠ እስካሁን ይፋ አልተደረገም፤ ነገር ግን አሶሼትድ ፕረስ እና ሲኤንኤን ጥቆማውን የሰጠው እራሱ ተጠርጣሪው እንደሆነ እየዘገቡ ይገኛሉ።
ተጠርጣሪው ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ የሚባል ከሆነ የተለያዩ የፌደራል ሕጎችን በመጣስ እስከ እድሜ ልክ የሚደርስ ቅጣት ሊጠብቀው ይችላል። ከዚህ በፊት 9 ጊዜ በቁጥጥር ስር ውሎ እንደነበርም ፖሊስ አስታውቋል።
ምንም እንኳን በባቡር ጣቢያው ጥቃት ወቅት ሁለት ካሜራዎች በመበላሸታቸው ተጠርጣሪውን መለየት አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም ለመንቀሳቀሻ የተከራየው መኪና ቁልፍ በቦታው ላይ መገኘቱን ተከትሎ ነው ተጠርጣሪውን መከታተል የተቻለው።
የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ እንዳስታወቀው ተጠርጣሪው ሰኞ ዕለት ፊላደልፊያ ውስጥ ተሽከርካሪውን ከተከራየ በኋላ በቀጣዩ ቀን ወደ ኒው ዮርክ እየነዳ ገብቷል።
ተጠርጣሪው ፍራንክ ጄምስ ዛሬ ሐሙስ ኒው ዮርክ የሚገኝ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ይጠበቃል።
ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ፍራንክ ጄምስ ዊስኮንሲን እና ፊላደልፊያ ውስጥ አድራሻው የተገኘ ሲሆን በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቹ በኩልም አንዳንድ የትችት አስተያየቶችን ይሰጥ ነበር ተብሏል።
ከዚህ በፊትም የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ኤሪክ አዳምስን በተመለከተም ትችት ይሰነዝር እንደነበር ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
እንደ ፖሊስ መግለጫ ከሆነ ጥቃት አድራሹ ግለሰብ ሁለት የጭስ ፈንጂዎችን ካፈነዳ በኋላ ብሩክሊን የሚገኘው ባቡር ጣቢያ ውስጥ የተኩስ እሩምታ ከፍቷል። በጥቃቱ ጥቅም ላይ የዋለው የጦር መሳሪያም 'ግሎክ 9 ሚሊሜትር' የተሰኘ ሽጉጥ ሲሆን ግማሽ አውቶማቲክ እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል።
ጥቃቱን ተከትሎ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ባጋሯቸው ምስሎች ላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው መሬት ላይ ወድቀው እንዲሁም በጭስ ታፍነው ታይቷል። በጥቃቱ ተጨማሪ 13 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ጉዳታቸው ከከባድ ጭስ፣ በግፊያ መሀል ከመውደቅና ከከባድ ድንጋጤ ጋር የተያያዙ ናቸው።












