መልስ ያላገኘው ከናይሮቢ ጎዳና ላይ ታፍኖ አድራሻው የጠፋው ኢትዮጵያዊ ጉዳይ

የፎቶው ባለመብት, family
ከአራት ወራት በፊት በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ውስጥ አንድ መንገደኛ የቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምስል የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ተንቀሳቃሽ ምስሉ ኢትዮጵያዊው ሳምሶን ተክለ ሚካኤል በጠራራ ፀሐይ ከናይሮቢ ጎዳና ላይ ታፍኖ ሲወሰድ ያሳያል በሞባይል ስልክ የተቀረጸ ቪዲዮ ነበር።
ዘወትር በትራፊክ ከሚጨናነቁት የናይሮቢ ጎዳናዎች መካከል ኦሊቶክቶክ ተብሎ በሚጠራው መንገድ ላይ፤ ሳምሶን ሲያሸከረክር ከነበረው ዘመናዊ መኪና ውስጥ ቁጥራቸው በዛ ባሉ ሰዎች በኃይል ተጎትቶ ወርዶ ወደ ሌላ መኪና በኃይል እንዲገባ ሲደረግ ያሳያል ይህ በስፋት የተጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል።
በዚህ ቪዲዮው ላይ ሳምሶን ወደ አጋቾቹ መኪና ላለመግባት ሲታገል ይታያል። ሲጮህም ድምጹ ይሰማል። ሁኔታውን አላፊ አግዳሚው በአንክሮ ይመለከታል። የተቀረው ሁኔታውን በሞባይል ስልኩ ይቅርጻል። በሰተመጨረሻም ሳምሶን እና አጋቾቹን የያዘችው መኪና በፍጥነት ከአካባቢው ተሰወረች።
ይህ ከሆነ አራት ወራት አለፉ። ለሳምሶን ባለቤት እና ልጆቹ ምላሽ የሚሰጥ ጠፋ። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና የሳምሶን ቤተሰብ አባላት የኬንያ ፖሊስ ምንም ምላሸ አልሰጠንም ይላሉ።
የሳምሶን ባለቤት ሚለን መዝገቦ ጭንቅ ላይ ነች። ሚለን ክስተቱ መላ ቤተሰቡን ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ እንደከተተው ትናገራለች።
ልጆቿ ስለ አባታቸው ጥያቄ ከመጠየቅ እንደማያቆሙ ትናገራለች። ሳምሶን የታገተበትን ሁኔታ የሚያሳየው ምስል "ቤተሰቡ በየትኛውም ሰዓት ደኅንነቱ ሳይጠበቅ እንደሚኖር የሚያስታውስ ነው" ትላለች ሚለን።

"ልጆቼ በየዕለቱ እንደተሰቃዩ ነው። አባታቸው ከመኪናው ተጎትቶ በሌላ መኪና ሲወሰድ የሚያሳየውን ቪዲዮን አይተውታል" የምትለው ሚለን፤ እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ከኬንያ መንግሥት ምላሽ እንዳላገኘች ትገልጻለች።
"ማንም አልደወለልኝም። ለኪሊማኒ ፖሊስ ጣቢያ ቃሌን ከሰጠሁ በኋላ አንድም ያነጋገረኝ ፖሊስ የለም" ትላለች።
በኬንያ ላለፉት 17 ዓመታት የኖረው የትግራይ ተወላጁ ኢትዮጵያዊው ሳምሶን ፤ ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ ጋዝ በመላክ የንግድ ሥራ ላይ ነው የተሰማራው።
የኬንያ መንግሥት የሳምሶን አድራሻ በሚመለከት ምርመራውን እንዲያፋጥን የኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ አቅርቧል። በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም የኬንያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ምርመራ እያደረገ ከመሆኑ ውጪ ጉዳዩን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል ይላሉ።
"የአገሪቱ ፖሊስ ምርመራውን እስኪያጠናቅቅ ድረስ እንድንጠብቅ ነው ለኤምባሲው የተሰጠው ምላሽ። ተጨማሪ መረጃ እናገኛለን ብለን እንጠብቃለን" ሲሉ አምባሳደር መለስ ዓለም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ለኬንያ መንግሥት ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።
በኬንያ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች በአገሪቱ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ሰዎችን በኃይል የመሰወር ተግባር ተበራክቷል ይላሉ።

የአገሪቱ ፖሊስ በዚህ የሰዎች እገታ ላይ ተሳትፎ አለበት ተብሎ ክስ ይቀርብበታል። የፖሊስ ቃል አቀባዩ ግን በዚህ አይስማሙም።
ቃል አቀባዩ ብሩኖ ሺኦሶ ኢትዮጵያዊው ሳምሶን ተክለ ሚካኤል የት እንደሚገኝ እንደማያውቅ እና ጉዳዩን እየመረመረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
"የዜጎቻችንንና በግዛታችን ያለን የየትኛውንም ሰው ሕይወት መጠበቅ ኃላፊነታችን ነው። ለሌሎች፤ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል የሚመስል ድርጊት በፖሊስ የተደረገ ሊመስላቸው ይችላል። በጣም ንቁ የሆኑ ወንጀለኞች አሉ፤ የተለያዩ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ፤ ፖሊስ አይደለም፤ ፖሊስ ሊሆን አይችልም" ሲሉ ሳሙኤል በፖሊስ ታፍኗል ለሚለው ክስ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሳምሶን በአጋቾቹ ሲታፈን በሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ የኬንያ ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሰ ግለሰብ ይታያል።
የፖሊስ ቃል አቀባዩ ይህ በቪዲዮ ላይ የታየው የሕግ አስከባሪ አባል፤ የትራፊክ ፖሊስ አባል መሆኑን እና ለሌላ ኃላፊነት ተሰማርቶ እንደነበረ ይናገራሉ።
"ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ደብዳቤ ለማምጣት እና ለማድረስ ነው የወጣው። ጉዳዩ ምን እንደሆነ ለማጣራት ብቻ በቦታው የቆመ የፖሊስ አባል ነው" በማለት ይህ የሕግ አስከባሪ አባል፣ ሰው በቁጥጥር ሥር ለማዋልም ሆነ እርዳታ ለመስጠት በቦታው እንዳልተገኘ ገልጸዋል።
በቅርቡ የሳምሶን የቤተሰብ አባላት፣ በኬንያ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ሳሙኤል ያለበትን በተመለከተ የአገሪቱ መንግሥት መረጃ እንዲሰጥ የሚጠይቅ ሰልፍ አካሂደዋል።
እስካሁን ግን ለዚህ ጥያቄ ምንም አይነት ምላሽ አልተገኘም።














