በናይሮቢ የታፈነው የሳምሶን ባለቤት ጉዳዩ እጅጉን አሳስቦኛል አለች
ከቀናት በፊት በኬንያ ናይሮቢ የታፈነው ኢትዮጵያዊ ሳምሶን ተ/ሚካኤል ጉዳይ እጅጉን እንዳሳሰባት ባለቤቱ ሚለን ሃለፎም ለቢቢሲ ተናግራለች።
ሚለን ባለቤቷ ሕዳር 10 ነዋሪ በሆኑባት ናይሮቢ ከተማ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ከመንገድ ላይ በኃይል ከተወሰደ በኋላ አድራሻው አለመታወቁን ተናግራለች።
መንገደኛ ቀርጾት በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተሰራጨ ተንቀሳቃሽ ምስል፤ የትራፊክ ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሰ ግለሰብ ባለበት ሲቪል የለበሱ ሰዎች ሳምሶን ተ/ሚካኤልን ሲያሸከረክረው ከነበረው መኪና በኃይል ጎትተው ወደ ሌላ መኪና ሲከቱት አሳይቷል።
የባለቤቷን መታፈንን ተከትሎ ለኬንያ ፖሊስ እና ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳዩን ማሳወቋን የምትናገረው ሚለን፤ ናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትብብር እያደረገለት እንደሆነ ገልጻ "የኬንያ መንግሥት ግን እየተባበረ አይደለም" ብላለች።
የኬንያ ፖሊስ በበኩሉ ጉዳዩን እየተከታተለው እንደሆነ ገልጿል።
ሚላን ባለቤቷ በጋዝ ሽያጭ የንግድ ሥራ ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ እና ከዚህ ቀደም ዛቻም ሆነ ማስፈራሪያ ደርሷቸው እንደማያውቅ ጨምራ ተናግራለች።