የአርሶ አደሮችን ሕይወት ለማቅለል ዘመናዊ ጎተራ የሠራችው ወጣት

ደራርቱ ደረጀ

ደራርቱ ደረጀ በጅማ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ውስጥ የባዮ ሜዲካል ትምህርት ክፍል መምህርት ናት።

እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪዋን ባዮ ሜዲካል ኢሜጂንግ በሚባል የትምህርት ዘርፍ እየተማረች ሲሆን፣ ከትምህርቷ ጎን ለጎን ፈጠራዎች ላይ ተሰማርታለች።

ከሥራዎቿ መካከል አንዱ የሆነው ደግሞ አርሶ አደሮችን መሠረት በማድረግ የሠራችው ዘመናዊ ጎተራ ነው።

"ገበሬዎቻችን የሚጠቀሙበት ጎተራ ከጭቃ አልያም ከአፈር ስለሚሠራ የታፈነ ነው። በዚህም ምክንያት እህሉ በነቀዝ እንዲበላ ይሆናል" ትላለች ደራርቱ።

ደራርቱ አርሶ አደሮች የሚጠቀሙበት ባሕላዊው ጎተራ ምርታቸውን እንዲባክን ያደርጋል በማለት፣ ይህ ችግርም የከፋ እና ገበሬዎቹን ለምግብ ዋስትና እጥረት የሚያጋልጥ ነው ትላለች።

የዓለም የምግብ ድርጅት፣ እያደጉ ባሉ አገራት ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮች ከየሚያመርቱት ምርት፣ 40 እጅ ያህሉ ከማጠራቀሚያ ቦታ እጥረት የተነሳ እንደሚባክን ይገልጻል።

አስተማማኝ የእህል ማጠራቀሚያ አለመኖር ደግሞ አርሶ አደሮች ጉልበት እና ጊዜያቸውን የፈጁበት ምርት በተባይ እንዲበላ እና በእርጥበት ምክንያት ለብልሽት እንዲጋለጥ ያደርጋል።

ይህ የእህል ብክነትም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን ለምግብ ዋስትና ችግር እንዲጋለጡ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ቀዳሚው ነው።

ብዙ አርሶ አደሮች የሚጠቀሙበት ጎተራ ከእንጨት እና ከጭቃ የተሰራ መሆኑን የምትናገረው ደራርቱ "ብዙ አርሶ አደሮች ይቸገራሉ። እህላቸውን ነቀዝ ይበላዋል" ትላለች ደራርቱ።

የ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምርት ማከማቻው አሰራር ነፍሳት ወደ ጎተራው በቀላሉ በመግባት እህል ውስጥ እንዲራቡ እንደሚያደርገቸውም ታስረዳለች።

በተጨማሪም ይህ በባህላዊ መንገድ የሚሠራ ጎተራ፣ እንደ ልብ አየር ስለማይዘዋወርበት በውስጡ ያለው ሙቀት እንደ ነቀዝ ላሉ ነፍሳት መራቢያነት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

"የኢትዮጵያ ገበሬዎች አሁን እየተጠቀሙበት ያለው ጎተራ፣ ነፍሳት ውስጥ ገብተው በቀላሉ እህሉን እንዲያበላሹት ያስችላቸዋል። ስለዚህም ገበሬዎቹ ከሚያመርቱት 44.7 በመቶ ያህሉ በዚህ ሁኔታ ይባክናል" ስትል ታስረዳለች።

ዘመናዊው ጎተራ

ደራርቱ ይህንን የአርሶ አደሮች ችግር መሠረት በማድረግ አልሙኒየም በመጠቀም ዘመናዊ ጎተራ መስራቷን ትናገራለች።

ይህ ከአልሙኒየም የተሰራው ጎተራ ነፍሳት ወደ ጎተራው በቀላሉ እንዳይገቡ የሚከላከል መሆኑንም ታስረዳለች።

ይህ ጎተራ "አየር እንዲያስገባ ሆኖ ነው የተሰራው። ይህም ጎተራ ውስጥ ሙቀት እነዳይፈጠር ይረዳል። ነፍሳት ወደ ጎተራው ቢገቡ እንኳ ቶሎ እንዲሞቱ ያደርጋቸዋል" በማለት ታስረዳለች።

አየር ወደ ጎተራው እንዲገባ የሚያደርገው መላ የባትሪ ኃይልን በመጠቀም የተሰራ ነው። "ለወደፊቱ ግን የፀሐይ ብርሃንን በመጠቀም እንዲሰራ ለማድረግ እያሰብን ነው" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ደራርቱ የሠራችው ይህ ዘመናዊ ጎተራ አነስተኛ የሚባለው እስከ 50 ኪሎ መያዝ የሚችል ሲሆን፣ በሰዎች ፍላጎት ላይ በመመስረት ትልልቅ ጎተራዎችን መስራት ይቻላል።

ደራርቱ ይህንን ጎተራ ለመስራት ወጪውን ራሷ መሸፈኗን ገልጻ፣ በሥራው ላይ ግን የሚያማክራት ሰው እንዳለ ትናገራለች።

በሌላ በኩል ይህ ፕሮጀክት በተፈለገበት መልኩ ሥራ ላይ እንዳይውል እንቅፋት የሆነባት የገንዘብ ችግር መሆኑን በማንሳትም፣ ይህንን ለመቅረፍ የተለያዩ ውድድሮች ላይ እየተሳተፈች ነው።

በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት 'ቶታል ኢነርጂስ ስታርት አፐር' የሚባል ውድድር ላይ የመጀመሪያውን ዙር ማለፏን ትገልጻለች።

"አሁን ማነቆ የሆነብን የገንዘብ እጥረት ነው። ይህንን ውድድር ካለፍን በቀላሉ ገበሬዎቻችን ጋር መድረስ እንችላለን" ብላለች ደራርቱ።