በእስራኤል ከሚፈጸሙ ዘር ተኮር ጥቃቶች አብዛኞቹ ቤተ-እስራኤላውያን ላይ እንደሚያነጣጥሩ ሪፖርት ጠቆመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል ውስጥ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከተመዘገቡት የዘረኝነት ጥቃቶች ግማሽ ያህሉ ቤተ-እስራኤላውያን እንዲሁም አረቦች ላይ ያነጣጠሩ እንደነበሩ በመንግሥት የወጣ ሪፖርት አመለከተ።
የእስራኤል የፍትሕ ሚኒስቴር ባወጣውን ሪፖርት መሠረት እንደ አውሮፓውያኑ በ2021 እስራኤል ውስጥ ከተፈጸሙ 458 ዘር ተኮር ጥቃቶች መካከል 48 በመቶው ያህሉ የደረሱት ከኢትዮጵያ በሄዱ ቤተ-እስራኤላውያን እና በአረቦች ላይ ነው።
በእስራኤል የፍትሕ ሚኒስቴር ሥር የሚገኘው የዘር ተኮር ጥቃቶች መከላከል ክፍል እንዳለው እነዚህ ጥቃቶች በአገልግሎት ዘርፍ የሚስተዋል መድልዎ፣ የሥራ ቅጥር መድልዎ፣ ዘረኛ ንግግሮች እና ዘረኛ ማስታወቂያዎችን ያካትታሉ።
አምና ለእስራኤል የፍትሕ ሚኒስቴር በደረሱ ጥቆማዎች መሠረት ኢትዮጵያዊ የዘር ሐረግ ያላቸው እስራኤላውያን ዘረኛ መድልዎ ይደርስባቸዋል፣ ይገለላሉም።
በመሥሪያ ቤቱ ከተመዘገቡ ዘረኛ ጥቃቶች መካከል 24 በመቶው በቀጥታ ቤተ-እስራኤላውያን ላይ ሲያነጣጥሩ፣ ቀሪው 24 በመቶ አረቦች፣ 10 በመቶው ደግሞ የመካከለኛው ምሥራቅ የዘር ግንድ ያላቸው አይሁዳውያን ላይ የተቃጡ ናቸው።
የእስራኤል የፍትሕ ሚኒስቴር ባወጣውን ሪፖርት መሠረት፤ እአአ በ2019፤ 497 ዘር ተኮር ጥቃቶች ተመዝግበዋል። በ2020 ደግሞ 506 እንዲሁም አምና የተመዘገቡት 458 ጥቃቶች ናቸው።
እነዚህ ጥቃቶች በፍትሕ ሚኒስቴር የተመዘገቡ ብቻ ሲሆኑ፣ በመላው አገሪቱ ያለው እውነታ ከዚህ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ዘገባዎች ይጠቁማሉ።
በሪፖርቱ ላይ እንደተጠቀሰው ቤተ እስራኤላውያን ላይ ከሚደርሰው ጥቃት 23 በመቶው አገልግሎትን ያማከለ መድልዎ ሲሆን፣ 11 በመቶው ደግሞ የሥራ ቅጥር መድልዎ ነው።
በተጨማሪም 10 በመቶ በአደባባይ የሚሰነዘር ዘረኛ ንግግር፣ 9 በመቶ ዘረኛ ማስታወቂያ፣ 7 በመቶ ዘረኛ በሕዝብ አገልግሎት መስጫ የሚደረግ ንግግር፣ 7 በመቶ በፖሊስ የሚደርስ እንግልት፣ 4 በመቶ ትምህርትን ያማከለ ቅሬታ እንዲሁም 3 በመቶ ዘርን ያማከለ የወንጀል ጥቃት ይገኙበታል።

የፎቶው ባለመብት, ISRAEL PRIME MINISTER'S OFFICE
ፍትሕ ሚኒስቴር የመዘገባቸው ዘረኛ ጥቃቶች
የፍትሕ ሚኒስቴር ከመዘገባቸው ቤተ እስራኤላውያን እና የአረብ የዘር ሐረግ ያላቸው ሰዎች ላይ የደረሱ ዘረኛ ጥቃቶች ሦስቱን እንደ ማሳያ እንውሰድ።
አንደኛው ዩቫል መኩሪያ በተባለ ኢትዮ- እስራኤላዊ ላይ የደረሰ ነው።
ቪክትሪ የተባለ መደብር ውስጥ በቆዳ ቀለሙ ምክንያት በተደጋጋሚ መድልዎ እንደሚደርስበት በመግለጽ፣ ገጠመኙን በተንቀሳቃሽ ምስል ቀርጾ በፌስቡክ አጋርቷል።
ፍትሕ ሚኒስቴር ቪድዮውን ካየ በኋላ መደብሩን በፍርድ ቤት ከሶ፣ መደብሩ ለዩቫል 23,000 ዶላር እንዲከፍል ዳኛ ወስኗል።
ሁለተኛው ማሳያ መነሻቸው ምዕራብ እስያ የሆነው ድሩዜ የተባለው ማኅበረሰብ አባላት የሆኑ ጥንዶች ላይ የደረሰው ዘረኛ ጥቃት ነው።
ጥንዶቹ በውትድርና እስራኤልን ቢያገለግሉም ከጆሀንስበር ወደ እስራኤል ለመመለስ አውሮፕላን ሲጠብቁ በፀጥታ ተቆጣጣሪዎች ዘረኛ ንግግር ተሰንስሮባቸዋል።
ሦስተኛው ማሳያ በአውቶብስ ውስጥ አረቦችን ለይቶ የደረሰ መድልዎ ነው።
የኮቪድ-19 ክልከላዎችን ለማስጠበቅ የተሰማራ ኃይል በአንድ አውቶብስ እየተጓዙ የነበሩ አይሁዳውያንን ሳይቀጣ አረቦችን ግን ለይቶ "የመቀመጫ ቀበቶ አላሰራችሁም" በሚል ቀጥቷቸዋል።
ጉዳዩ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ የተጣለባቸው ቅጣት ተሰርዞ ፖሊሶቹ ተቀጥተዋል።
ዘረኝነት በእስራኤል
እስራኤል ውስጥ የሚደርስ ዘር ተኮር ጥቃት ከማንኛውም ዜጋ በላይ ከኢትዮጵያ በሄዱ ቤተ-እስራኤላውያን ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የአገሪቱ የፍትሕ ሚኒስቴር ሪፖርት ይገልጻል።
እስራኤል ውስጥ ቤተ እስራኤላውያን እንዲሁም ሌሎችም አፍሪካውያን ብሎም አረቦች መድልዎ እና መገለል እንደሚደርስባቸው የመለክታል።
ቤተ እስራኤላውያን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸው፣ ገፋ ሲልም ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸውም አይዘነጋም።
ፖሊስ ከመጠን ያለፈ ኃይል ከመጠቀም አንስቶ ቤተ-እስራኤላውያንን እስከ መግደል የደረሰባቸው አጋጣሚዎች ይታወሳሉ።
ኢትዮጵያውያን እስራኤላውያን በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት እንዲሁም በሌሎችም ማኅበራዊ ክንውኖች መድልዎ እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
በተለይም እስራኤል መግባት የዓመታት ሕልማቸው የነበረ ኢትዮጵያውያን የአይሁድ ሃይማኖት ተከታዮች ስለ ዘር ተኮር ጥቃቱ በተደጋጋሚ የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
የእስራኤል የፍትሕ ሚኒስትር ባወጣውን ሪፖርት መሠረት ከቤተ-እስራኤላውያን በተጨማሪ አረብ-እስራኤላውያን መድልዎ ይደርስባቸዋል።
ሪፖርት እንደሚያሳየው ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑ አረቦች ዘረኛ ጥቃት ይገጥማቸዋል አልያም ዘር ተኮር ጥቃት የደረሰበት ሰው ያውቃሉ።
ከእነዚህ መካከል 77 በመቶ የሚሆኑት ዘረኛ ጥቃት ሲደርስባቸው ሪፖርት አያደርጉም። ለዚህም ምክንያቱ ለውጥ ይመጣል ብለው አለማመናቸው ነው።
ለዘመናት በሰሜን ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪ የነበሩት ቤተ-እስራኤላውያን የአይሁድ እምነት ተከታዮች ሲሆኑ፣ በደርግ አስተዳደር የመጨረሻ ዓመታት የእስራኤል መንግሥት ባዘጋጃቸው ምስጢራዊ የአየር በረራዎች በሺዎች የሚቆጠሩት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አስራኤል መግባታቸው ይታወሳል።
በአስራኤል የስለላ ተቋም ሞሳድ መሪነት በግዙፎቹ የሰሎሞን እና የሙሴ ምስጢራዊ ተልዕኮዎች አማካይነት ሱዳን ውስጥ በተዘጋጀ ድብቅ የአየር ማረፊያ በኩል ነበር የመጀመሪያዎቹ ቤተ-አስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ያቀኑት።
ከዚያ በኋላም ቤተ-አስራኤላውያኑ ተመዝግበው አስፈላጊው ማጣራት በእስራኤል መንግሥት በኩል እየተከናወነ በሕጋዊ መንገድ የጉዞ ሂደታቸው እያከናወኑ ይገኛሉ።
ምንም እንኳን ቀደም ሲል ወደ አስራኤል የገቡት ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ችግሮች እየገጠሟቸው መሆኑን በተደጋጋሚ ቢገልጹም፣ አሁንም ወደ አስራአኤል ለመጓዝ የሚጠባበቁ እንዳሉ ይነገራል።
የዘር ጥቃትና ሌሎችም ፈተናዎች የገጠሟቸው ከኢትዮጵያ የሄዱ ቤተ-እስራኤላውያን የመኖራቸውን ያህል በተለያዩ መስኮች በእስራኤል ውስጥ ለስኬት የበቁም እንዲሁም በአገሪቱ ጦር ኃይል ውስጥ፣ በሚኒስትርነት እና ለሌሎችም ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች የበቁም አሉ።















