20 ሰዎች ከተጎዱበት የኒው ዮርኩ የባቡር ጥቃት ጋር በተያያዘ ፖሊስ አንድ ተጠርጣሪ ይፋ አደረገ

ፖሊስ እንዳለው ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ግንኙነት እንዳለው የተጠረጠረው ፍራንክ ጄምስ የተባለ የ62 ዓመት ግለሰብ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA/NEW YORK CITY POLICE DEPARTMENT

የምስሉ መግለጫ, ፖሊስ እንዳለው ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ግንኙነት እንዳለው የተጠረጠረው ፍራንክ ጄምስ የተባለ የ62 ዓመት ግለሰብ ነው

በአሜሪካዋ ኒው ዮርክ ባቡር ጣቢያ ውስጥ እንድ ግለሰብ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ከ20 በላይ ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ፖሊስም ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ የአንድን ግለሰብ ስም ይፋ አድርጓል።

ፖሊስ እንዳለው ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ግንኙነት እንዳለው የተጠረጠረው ፍራንክ ጄምስ የተባለ የ62 ዓመት ግለሰብ ነው።

እስካሁንም ጥቃት አድራሹ ለመንቀሳቀሻነት የተከራየውን ተሽከርካሪ ፖሊስ ማግኘት ችሏል።

የተሽከርካሪው ቁልፍ ደግሞ ጥቃቱ የደረሰበት አካበቢ የተገኘ ሲሆን ግለሰቡ መኪናውን የተከራየው ፊላደልፊያ ውስጥ ነው ተብሏል።

"ከባቡር ጣቢያው ጋር እንዴት ግንኙነት እንዳለው ለማወቅ እየጣርን ነው'' ብለዋል የኒውዮርክ ፖሊስ መርማሪዎች ኃላፊው ጄምስ ኤሲግ።

አክለውም ስለተጠርጠሪው ግለሰብ ማንኛውም ዓይነት መረጃ ያለው ሰው ለፖሊስ እንዲያጋራ ጠይቀዋል።

ምንም እንኳን ፖሊስ ግለሰቡን ጥቃቱን በማድረስ ተጠርጠሪ ነው ብሎ ባይደመድምም ከምርመራው ጋር በተያያዘ ግን የሚፈለግ ነው ብሏል።

ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ፍራንክ ጄምስ ዊስኮንሲን እና ፊላደልፊያ ውስጥ አድራሻው የተገኘ ሲሆን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ በኩልም አንዳንድ የትችት አስተያየቶችን ይሰጥ ነበር ተብሏል።

ከዚህ በፊትም የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ኤሪክ አዳምስን በተመለከተም ትችት ይሰነዝር እንደነበር ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

እንደ ፖሊስ መግለጫ ከሆነ ጥቃት አድራሹ ግለሰብ ሁለት የጭስ ፈንጂዎችን ካፈነዳ በኋላ ብሩክሊን የሚገኘው ባቡር ጣቢያ ውስጥ የተኩስ እሩምታ ከፍቷል።

በጥቃቱ ጥቅም ላይ የዋለው የጦር መሣሪያ ግሎክ 9 ሚሊሜትር የተሰኘ ሽጉጥ ሲሆን ግማሽ አውቶማቲክ እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል።

"ሽጉጡን 33 ጊዜ ተኩሷል። በዚህም ወቅት ጥይቶቹ 10 ሰዎችን ጎድተዋል'' ብለዋል ኃላፊው ጄምስ ኤሲግ።

ጥቃቱን ተከትሎ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ባጋሯቸው ምሥሎች ላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው መሬት ላይ ወድቀው እንዲሁም በጭስ ታፍነው ታይቷል።

በጥቃቱ ተጨማሪ 13 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ጉዳታቸው በከባድ ጭስ ከመታፈን፣ በግፊያ መሀል ከመውደቅና ከከባድ ድንጋጤ ጋር የተያያዙ ናቸው።

በአጠቃላይ ግን ሁሉም ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ለሕይወታቸው የሚያሰጋ እንዳልሆነ ተዘግቧል።

"ጥቃት አድራሹ ወዲያው ከአካባቢው ተሰውሯል። መርማሪዎች ወዴት እንደሄደ ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው የሚገኙት'' ብለዋል የፖሊስ ኃላፊው።

ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በሚደረገው ጥረት ትክከለኛውን መረጃ ለሚያቀብል ሰው 50 ሺህ ዶላር ተዘጋጅቷል።

እስካሁን ተጠርጣሪው ለምን ጥቃቱን እንደሰነዘረ የታወቀ ነገር የለም።

የኒው ዮርክ ፖሊስ ኮሚሽነር ኪቻንት ሴዌል በበኩላቸው እስካሁን ድረስ ጥቃቱ ከሽብር ጥቃት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ተጨባጭ መረጃ አላገኝንም ብለዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ባስተላለፉት መልዕክት ጉዳት የደረሰባቸውን ለመርዳት በቦታው በቶሎ የደረሱትን የፖሊስና የሕክምና እርዳታ ሰጪዎችን ያመሰገኑ ሲሆን በአካባቢው የነበሩ ሰዎችም ላደረጉት ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።