በምሥራቅ ዩክሬን ዶንባስ የሚደረገው ጦርነት ደም አፋሳሽ እንዳይሆን ተፈርቷል

የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ወደ 2ኛ ወሩ እየተጠጋ ነው፡፡
ሩሲያ በሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮችን አጥታለች፡፡ በርካታ ጄኔራሎችም ተገድለውባታል፡፡
ዋና ከተማ ኪየቭን በአጭር ቀናት የመቆጣጠሩ ነገር አልሆነላትም፡፡
አሁን ኪየቭን የከበበው የሩሲያ ጦር ሙሉ በሙሉ ለቋል፡፡
ቭላድሚር ፑቲን፣ ከዚህ በኋላ ትኩረታችን በምሥራቅ ዩክሬን ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አዲስ ጄኔራልም ሾመዋል፡፡
ይህን ተከትሎም እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊታቸው ወደ ምሥራቅ ዩክሬን እየገሰገሰ ነው፡፡
የዶንባስ ክልል አካል የሆነችው ቁልፏ የወደብ ከተማ ማሪዮፖል አልህ አስጨራሽ ጦርነት እየተደረገባት ይገኛል፡፡
በቀጣይ ቀናት በሩሲያ እጅ ልትወድቅ ትችላለች የሚሉ በርካታ ናቸው፡፡
በዚያ የሚገኙ የዩክሬን ተዋጊዎች ወደ 4ሺህ የሚጠጉ ሲሆን የሩሲያ ጦር ግን የዚህን ሦስት እጥፍ ይሆናል፡፡
የማሪዮፖል ከንቲባ በዚያች ከተማ በሩሲያ ወታደሮች የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር 21ሺህ ይጠጋል ሲሉ ትናንት ተናግረዋል፡፡
በዘግናኝና ኢሰብአዊ ሁኔታ የተገደሉ ዩክሬናዊያንም ሬሳዎቻቸው በድበቅ ቦታ በጅምላ እየተቀበረ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
ማሪዮፖል እንደተፈራው በቀጣይ ቀናት በሩሲያ እጅ ከወደቀች ዶንባስ ክልል ዙርያውን ከበባ ውስጥ ይገባል የሚል ፍርሃት አለ፡፡
ዞሮ ዞሮ በቀጣይ ቀናት እና ሳምንታት በምሥራቃዊ ዩክሬን የሚኖረው ጦርነት ከእስከዛሬው ሁሉ የከፋና እልህ አስጨራሽ እንዲሁም ደም አፋሳሽ እንደሚሆን ከወዲሁ እየተነገረ ነው፡፡
ለዚህም ይመስላል ዩክሬናዊያን ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ከዶንባስ ክልል ለመሸሽ እየተሸቀዳደሙ ያሉት፡፡
ሰዎች ብቻ ሳይሆን ዉሾች እንኳ የሚሆነውን የተረዱ ይመስላሉ፡፡ ከርቀት የተኩስ ድምጽ በሰሙ ቁጥር ጩኸታቸው ያሰማሉ፤ ያላዝናሉ፡፡
በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት ዩክሬናዊያን ምሥራቁን ክፍል ጥለው እየሸሹ ያሉት በብዛት ወደ ምዕራብ ዩክሬን ነው፡፡
እስከአሁን ወደ 4.6 ሚሊዮን የሚጠጉ ዩክሬናዊያን ውድ አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡

በዚህ ወቅት የሳተላይት ምሥሎች እንዳረጋገጡት የሩሲያ ሰራዊት በረዥም ሰልፍ ወደ ምሥራቅ እየተመመ ነው፡፡
የዩክሬን ሰራዊትም ሳይቀደም ለመቅደም ብረት ለበስ ተሸከርካሪዎችን፣ አየር መቃወሚያዎችን እና ሌሎች ከምዕራብ አገራት የተገኙ ውስብስብ የጦር መሣሪያዎችን ወደ ምሥራቅ በማጓጓዝ ተጠምዷል፡፡
ነገር ግን ከሩሲያ ሰራዊት ጋር ሲወዳደር ቁጥሩ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
በርካታ የጦር አዋቂዎች እንደሚሉት የምሥራቁ ጦርነት ወሳኝና አሸናፊ የሚኖር ከሆነም ያንኑ የሚለይ ይሆናል፡፡
ሁሉንም ተንታኞች ያስማማው ነጥብ ግን ይህ ጦርነት የዋዛ ጦርነት እንደማይሆን ነው፡፡
እጅግ ዘግናኝና ደማ አፋሳሹ ጦርነት ይኸው የምሥራቁ ጦርነት ነው ተብሎ ተፈርቷል፡፡
ቢቢሲ በዩክሬን ወታደሮች ፈቃድ የመከላከያ ምሽጎችን መመልከት የቻለ ሲሆን ወደ ስፍራው መድረስ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ብረት ለበስ ተሽከርካሪን በመጠቀም ነው፡፡
ቢቢሲ በስፍራው እንዳይቀርጽ የተከለከላቸው በርካታ የአየር መቃወሚያዎችን፣ ራዳርና ሮኬቶችንም ተመልክቷል፡፡
ሩሲያ ጄት ወይም ድሮኖችን ከላከች በሚል እነሱን ለመምታት የተፈበረኩና ከምዕራብ አገራት ለዩክሬን የተለገሱ ውስብስብ መሣሪያዎችንም ቢቢሲ ለመመልከት ችሏል፡፡
ሩሲያ እስከዛሬ በነበረው ጦርነት በአየር ኃይል የበላይነት ብትይዝም ይህ ግን ከዚህ በኋላ ዘላቂ ላይሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
ምክንያቱም አሁን ያገኘቻቸው መሣሪያዎች ዓይነትና ብዛት ነው፡፡
ሩሲያና ዩክሬን አሁን በስፍራው እያንዳንዳቸው ከ30 እስከ 40 ሺህ ሰራዊት እንደሚያሰልፉ ይጠበቃል፡፡
ሆኖም አንዳንድ ተንታኞች ሩሲያ በቅርብ ጊዜ ይህን የሰራዊት ቁጥር በሦስት እጥፍ እንደምታሳድግ ይናገራሉ፡፡
ሩሲያ ባለፉት ሳምንታት በተደረጉ ጦርነቶች የሰራዊቷን 20 ከመቶ አጥታለች የሚሉ ተንታኞች አሉ፡፡
በዚህም የተነሳ የሩሲያ ወታደሮች ላይ ብርታትና መነቃቃት አይታይም፤ እንደ ዩክሬናዊያን ለመዋጋት ሞራል የላቸውም ይላሉ የምዕራቡ ዓለም የጦር አዋቂዎች፡፡
የዩክሬናዊያን ወታደሮች ሞራልና የመዋጋት ፍላጎት በአንጻሩ ከፍ ያለ ነው፡፡
በጦርነቱ መሀል የምዕራብ አገራት አሜሪካን ጨምሮ ከፍተኛ የስለላና ደኅንነት ቁልፍ መረጃዎችን ወዲያውኑ ከዩክሬን ያቀብላሉ፡፡
ቢቢሲ ይህ እውነት ስለመሆኑ ከዩክሬንም ሆነ ከምዕራብ አገራቱ ማረጋገጫ አግኝቷል፡፡
ይህም ማለት የሩሲያ ሰራዊት እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ለዩክሬን ወቅታዊ መረጃዎች እንዲደርሷት አውሮጳና አሜሪካ ተግተው ይሠራሉ፡፡
ይልቅ ለዩክሬናዊያን ራስ ምታት የሆኑት ሩሲያ ያሰማራቻቸው ሰላዮችና አሻጥረኞች ናቸው፡፡
ቢቢሲ በክራማቶር ከተማ አንድ ፖሊስ ጣቢያ በርካታ የሩሲያ አሻጥረኞች ናቸው የተባሉ እስረኞችን ለመመልከት ችሏል፡፡
በዩክሬን ለሩሲያ ስስ ልብ ያላቸው በርካታ ዩክሬናዊያን በብዛት የሚገኙት በዚህ ዶንባስ ክልል ነው፡፡
ለዚህም ነው ፖሊስ በየመንገዱ ነዋሪዎችን እያስቆመ ተደጋጋሚ ፍተሻን የሚያደርገው፡፡
ፑቲን ትናንት ከቤላሩሱ አጋራቸው አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ጋር ተገናኝተው መክረዋል፡፡
አገራቸው በዚህ ጦርነት ድል እንደምታስመዘግብም ተናግረዋል፡፡ የሰላም ተስፋ እንደሌለም ጠቁመዋል፡፡
ሉካሼንኮ በበኩላቸው ቤላሩስ ምንጊዜም ከሩሲያ ጎን ትቆማለች ብለዋል፡፡
በቀጣዮቹ ሳምንታት ምናልባትም በአውሮጳ ታሪክ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ፈጽሞ ያልታየ እልቂት ሊኖር ይችላል እየተባለ ነው፡፡












