"በሩሲያ የነዳጅና እና ጋዝ ምርቶች ላይ ሙሉ እገዳ ቢጣል የዩክሬንን ጦርነት ሊያስቆመው ይችላል"

የፎቶው ባለመብት, Anadolu / Getty
ምዕራባውያን ሃገራት በሩስያ " የነዳጅና ጋዝ ምርቶች ላይ ሙሉ እገዳ ቢጥሉ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ሊያስቆመው እንደሚችሉ የፕሬዚዳንት ፑቲን የቀድሞ የምጣኔ ኃብት ዋና አማካሪ ተናገሩ።
ዶክተር አንድሬይ ኢላሪዮኖቭ እንዳሉት ሩሲያ የሌሎች ሃገራት የሀይል አጠቃቀማቸውን ለመቀነስ የሚያደርሱትን ዛቻ በቁም ነገር ሩሲያ እየተመለከተችው እንዳልሆነ ገልጸዋል።
በሩስያ ኃይል ምንጮች ላይ ያለውን ጥገኛነት ለመቀነስ ቢሞክርም በአሁኑ ወቅት አውሮፓ ነዳጅ እና ጋዝ መግዛቱን ቀጥሏል ብለዋል።
ባለፈው አመት የዋጋ ማሻቀቡን ተከትሎ ለሩሲያ መንግሥት የገባው የነዳጅ እና የጋዝ ገቢ 36 በመቶውን ወጪውን ሸፍኗል።
አብዛኛው ገቢ የሚገኘው ከአውሮፓ ህብረት ሲሆን፣ ህብረቱ 40 በመቶ የሚሆነውን ጋዝ እና 27 በመቶውን ዘይት የሚያስገባው ከሩሲያ ነው።
በዚህ ሳምንት የህብረቱ ከፍተኛ ዲፕሎማት የሆኑት ጆሴፕ ቦሬል "ፑቲን ለሚሰጠን ኃይል አንድ ቢሊዮን ዩሮ በየቀኑ እንከፍላለን" ብለዋል።
ዶክተር አንድሬይ ኢላሪዮኖቭ እንዳሉት "ምዕራባውያን አገሮች ከሩሲያ ወደ ውጭ በሚላኩ የነዳጅ እና የጋዝ ምርቶች ላይ እውነተኛ እቀባን ተግባራዊ ለማድረግ ቢሞክሩ ... ምናልባት በአንድ ወይም በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ የሩሲያ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በዩክሬን ይቆማሉ ብዬ እገምታለሁ ። " በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
"አሁንም በምዕራባውያን አገሮች እጅ ከሚገኙ በጣም ውጤታማ መሳሪያዎች አንዱ ነው" ሲሉም አክለዋል።
ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ የነዳጅ እና የጋዝ ንግዱ ቢቀጥልም፣ መጠነ ሰፊ ማዕቀቦች መጣላቻውን ተከትሎ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ቆመዋል፣ በርካታ የውጭ ኩባንያዎች ለቀው ወጥተዋል፤ እንዲሁም ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችም ተስተጓጉለዋል።
በቅርቡ የሩስያ ማዕከላዊ ባንክ ባደረገው አንድ ጥናት ኢኮኖሚው በዚህ አመት 8 በመቶ እንደሚቀንስ ሲተነብይ አለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም ደግሞ በ15 በመቶ ሊቀንስ ይችላል ብሏል።
ዶክተር አንድሬይ እንደሚሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን በኢኮኖሚው ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመቋቋም ዝግጁ መሆናቸው ቅድሚያ የሚሰጧቸው ጉዳዮች የት እንዳሉ እንደሚያሳይ ጠቁሟል።
"የግዛት ማስፋፋት ምኞቱ፣ የንጉሠ ነገሥታዊ ምኞቱ ከየሩስያ ሕዝብ መተዳደሪያ እና የአገሪቱን የፋይናንስ ሁኔታ ጨምሮ፣ እንዲሁም ከመንግሥቱን የፋይናንስ ሁኔታ ጨምሮ ከሁሉ ነገር በላይ ናቸው " ብለዋል።













