የኮቪድ-19 ክልከላ ጥሰው ድግስ የታደሙት ቦሪስ ጆንሰን ሥልጣን እንደማይለቁ አስታወቁ

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እና የፋይናንስ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ
የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እና የፋይናንስ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እና የፋይናንስ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ የኮቪድ-19 ክልከላ በመጣስ በፖሊስ የገንዘብ ቅጣት ቢጣልባቸውም ሥልጣናቸውን እንደማይለቁ አስታወቁ።

በሰኔ 2020 የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የወጣ በቡድን ያለመሰብሰብ መርህን ጥሰው መጠጥ በሚቀረብበት ድግስ ላይ በመገኘታቸው ፖሊስ በገንዘብ ሊቀጣቸው ወስኗል።

ፖሊስ የቦሪስ ጆንሰንን ባለቤት እንዲሁም የፋይንስ ሚኒስትሩን ቀጥቷል።

ባለሥልጣናቱ ወረርሽኙን ለመግታት የወጣ መርህ ጥሰው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ልደት በዶውኒንግ ስትሪት ድግስ አዘጋጅተዋል።

ቦሪስ ጆንሰን ሥልጣን ላይ ሳሉ ሕግ በመጣስ የተቀጡ የመጀመሪያው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል።

ባለሥልጣናቱ ስለ ድርጊታቸው ይቅርታ ቢጠይቁም ኃላፊነታቸውን እንደማይለቁ ተናግረዋል።

ቦሪስ ጆንሰን "የብሪታኒያ ሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት የበለጠ ተነሳስቻለሁ" ብለዋል።

አመራሮቹ መርህ መጣሳቸው "አሳፋሪ ነው" ያሉ ቤተሰቦቻቸውን በኮሮናቫይረስ ያጡ ሰዎች ግን ሥልጣናቸውን እንዲለቁ እየጠየቁ ነው።

በወረርሽኙ ወቅት ልጇ ኢዛቤል የሞተችባት አማንዳ ማክጋን፤ ለልጇ ቀብር የሰዎች ቁጥር እንዲቀንስ ተደርጎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ድግስ ላይ በመገኘታቸው ማዘኗን ትናገራለች።

የሌበር ፓርቲ መሪ ሰር ኪር ስታርመር ባለሥልጣናቱ ከስልጣናቸው እንዲነሱ የጠየቁ የመጀመሪያው የተቃዋሚ መሪ ናቸው።

ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ባለሥልጣናቱ ሕዝቡን በመዋሸታቸው ኃላፊነታቸውን እንዲለቁ ጠይቀዋል።

የሜትሮፖሊታን ፖሊስ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የወጡ መርሆችን የጣሱ 12 ድግሶችን እየመረመረ ይገኛል።

እስካሁን 50 ሰዎች በገንዘብ የተቀጡ ሲሆን፤ ተጨማሪ ሰዎችም ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ተገልጿል።

ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው የልደት ድግሳቸው "ከ10 ደቂቃ ያልዘለለ" እንደነበር ተናግረዋል።

ሕዝቡ "ከኔ የተሻለ ነገር እንደሚጠብቅ አውቃለሁ" ሲሉም ቅጣቱን ተቀብለዋል።

"በወቅቱ መርህ እየጣስኩ እንደሆነ አላሰብኩም ነበር። ፖሊስ አጥፍተሀል ካለኝ ግን ውሳኔያቸውን አከብራለሁ" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤት ቃል አቀባይ ኬሪ ጆንሰን፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤትም የገንዘብ ቅጣታቸውን ተቀብለው ይቅርታ እንደጠየቁ ተናግራለች።

የፋይናንስ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ "የመንግሥት ባለሥልጣኖች ለሕዘብ የሚወጡ መርሆችን ማክበር እንዳለባቸው አምናለሁ። የተጣለብኝን የገንዘብ ቅጣት ከፍያለሁ" ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል።

የሌበር ፓርቲ ምክትል መሪ አንጅላ ሬይነር "እራሳችሁ ያወጣችሁትን ሕግ ነው የጣሳችሁት። ሥልጣን ልቀቁ" ሲሉ ትዊት አድርገዋል።

የግሪን ፓርቲ አጋር መሪ ኤድርያን ራምሲ "ሁለቱ አመራሮች የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ የወጣ መርህን ነው የጣሱት። ሥልጣናቸውን መልቀቅ አለባቸው" ብለዋል።

በሌላ በኩል ባለሥልጣናቱ በሥራ ኃላፊነታቸው መቆየት አለባቸው ብለው የተከራከሩ ፖለቲከኞችም አሉ።

የሥራና ጡረታ ሚኒስትር ቴሬሳ ኮፊ ከእነዚህ አንዷ ናቸው።

የሕዝን ተወካይ ምክር ቤት አባሉ ሰር ሮጀር ጌል ከዚህ ቀደም እነ ቦሪስ ጆንሰን ሥልጣን እንዲለቁ ቢጠይቁም፤ አሁን ግን ሩሲያ ዩክሬንን ከመውረሯ ጋር ተያይዞ "ጠቅላይ ሚኒስትር መቀየሪያ ጊዜ አይደለም" ብለዋል።