የእንግሊዙን ፓርላማ አባል የገደለው ግለሰብ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእንግሊዝ ፓርላማ አባል የነበሩትን ሰር ዴቪድ አሜስን የገደለው አሊ ሃርቢ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።
የአይኤስ አባል የሆነው አሊ በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ነው የሳውዝኢንድ ዌስት ተወካይ የሆኑትን የፓርላማ አባል ከ20 ጊዜ በላይ በስለት ወግቶ የገደላቸው።
በወቅቱም የፓርላማ አባሉ በኢሴክስ ግዛት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ውይይት እያደረጉ ነበር ተብሏል።
በዛሬው ዕለት በዋለው ኦልድ ቤይሊ ችሎት ላይ ዳኛው ስዊኒ " ይህ ግድያ የዲሞክራሲያችንን አከርካሪ የመታ ነው" ብለዋል።
የሟቹ ፓርላማ አባል ዴቪድ አሜስ ቤተሰቦች በበኩላቸው የሆነው ነገር "ከእኩይ ተግባር በላይ ነው" በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ተከሳሹ አሊም በዛሬው የፍርድ ውሎ ላይ "የካቢኔ ሚኒስትሩን ሚካኤል ጎቭን ጨምሮ የተለያዩ የፓርላማ አባላትን ኢላማ ያደረገ እቅድ ነበረኝ" ብሏል።
በሶሪያ ላይ የአየር ጥቃት እንዲፈጸም በመረጡ የፓርላማ አባላትንም ለመበቀል መነሳሳቱን አስረድቷል።
ግድያውን ለመፈጸም የብሔራዊ ጤና አገልግሎት ሰራተኛ ነኝ በሚል የ69 አመቱን የፓርላማ አባል በነበረው ስብሰባ ላይ እንዳገኛቸው ተገልጿል።












