ስደት፡ ዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳያቸውን ለማስፈፀም ወደ ሩዋንዳ ልትልክ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ስምምነት ልትፈርም መሆኑ ተገለጸ።
በዚህ እቅድ መሠረትም የተወሰኑ ጥገኝነት ጠያቂዎች ጥያቄያቸውን ለማቅረብና ለማስፈፀም ወደ ሩዋንዳ ይወሰዳሉ።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሪቲ ፓቴል ከአፍሪካዊቷ አገር ጋር የስደት ሰምምነት ከመፈራረማቸው በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እቅዶቹን ይፋ ያደርጋሉ ተብሏል።
የስደተኞች ምክር ቤት ፖሊሲውን " ጨካኝ" ሲል የተቸው ሲሆን በድጋሜ እንዲጤንም አሳስቧል።
ሌበር ፓርቲ በበኩሉ እቅዱ " የማይሰራ ፣ ሥነ ምግባር የጎደለው እና ምዝበራ ነው" ያለው ሲሆን እቅዱ የወጣው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ የኮቪድ-19 ሕጎችን በመጣስ ሊጣልባቸው የታሰበውን ቅጣት ለመሸፈን ነው ብሏል።
ይሁን እንጂ ሊበራል ዲሞክራቶች "አደገኛ ባህሮችን የሚሻገሩ ስደተኞችን ማስቆም ወይም ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ቡድኖችን መዋጋት ካልተቻለ ለግብር ከፋዮች ከባድ ሊሆን ይችላል" ሲል ገልጿል።
በእቅዱ መሠረት የሩዋንዳ መንግሥት ለሙከራ የሚውል የመጀመሪያ 120 ሚሊየን ፓውንድ ይሰጠዋል ተብሏል፤ ይሁን እንጂ ተቃዋሚዎች የሙሉ እቅድ አመታዊ ወጪው በጣም ከፍተኛ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት 28 ሺህ 526 ሰዎች ኢንግሊሽ ቻናል በትናንሽ ጀልባዎች ማቋረጣቸው የተገለጸ ሲሆን ይህ ቁጥር በ2020 8 ሺህ 404 ነበር።
ረቡዕ ዕለት ደግሞ 600 የሚጠጉ ሰዎች ማቋረጣቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሃዙ በሳምንት ውስጥ በቀን 1000 ሊደርስ ይችላል ብለዋል።
" ተመሳሳይ ሕገ ወጥ ሥርዓትን ማስቀጠል አንችልም፤ የእኛ ርህራሔ ላያልቅ ይችላል፤ ነገር ግን ሰዎችን የመርዳት አቅማችን እንደዚያ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የኢንግሊሽ ቻናል ቁጥጥሩን ለባሕር ኃይሎች ለማስረከብ ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን የንግድ ትስስር ለመበጠስና ሰዎችን አደጋ ላይ እንዳይጥሉ ለማድረግ እቅዱ ማስፈለጉን ገልጸዋል።
እርምጃዎቹም ከብሬግዚት በኋላ " ሕገ ወጥ ስደትን ለመቆጣጠር" የመንግሥት የረዥም ጊዜ እቅድ አካል ናቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ተናግረዋል።
የእንግሊሽ ቻናልን በጀልባ የሚያቋርጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም ፤ ባለፈው ዓመት ግን ጥቂት ሰዎች በወደብ በኩል ለመግባት ከባድ ተሽከርካሪዎችን እና ሌሎች መንገዶችን ሲጠቀሙ ተስተውሏል።












