እውቁ የአውሮፓን እግር ኳስ የሚዘውረው ቱጃር 'ደላላ' በሞት ተለየ

ሚኖ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"ሚኖ" በሚለው በመጀመሪያ ስሙ የሚጠራው እውቁ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ወኪል ሚኖ ራዮላ በ54 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል።

የሆላንድ እና ጣሊንያን ጥምር ዜግነት ያለው ሚኖ፤ እንደ የዶርትመንዱ የፊት መስመር ተጫዋች ሃላንድ፣ የማንችስተር ዩናይትዱ ፖል ፖግባ፣ ዝላታን ኢብራሂሞቪች፣ ሄንሪክ ሚኪታሪያንና ዴ ሊት የመሳሰሉ ተጨዋቾች ወኪል ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም ሚኖ እውቅ የተጫዋቾች ወኪሎችን የሚወክለው 'ፉትቦል ፎረም' ፕሬዝደንት ነበር።

ሕልፈተ ሕይወቱን ተከትሎ፤ 'ሚኖ ሁሌም ይናፈቃል' ሲሉ የሚኖ ቤተሰብ መግለጫ አውጥተዋል።

ሚኖ ማን ነበር?

ጣልያን ተወልዶ በኔዘርላንድስ ሃርለም ከተማ እንዳደገ የሚነገርለት ራዮላ ሁሉም የሚስማሙለት 'ምርጥ ደላላ' ነው።

በልጅነቱ አባቱ በከፈቱት ሬስቶራንት ውስጥ ደፋ ቀና ብሎ አስተናግዷል። በጎንዮሽ ደግሞ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በሕግ ተመርቋል።

ጣልያንኛ፣ ጀርመንኛ፣ ስፓኒሽ፣ ፈረንሳይኛ፣ ፓርቹጊዝ፣ ደች እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ የሚናገረው ራዮላ ገና የ18 ዓመት ለጋ ሳለ ነበር ኔዝርላንድስ ውስጥ የሚገኝ አንድ የታዳጊዎች እግር ኳስ ኃላፊ ሆኖ ራሱን ያገኘው።

ከዚያም የነብስ ጥሪው ወደሆነው የወኪልነት ሥራ ገባ፤ ለአንድ ወኪል ድርጅት ተቀጥሮ ይሠራም ጀመር። የመጀመሪያው ሥራ የሆነው ደግሞ ተስፋ የሚጣልባቸውን ታዳጊ ደች ተጫዋቾችን ለጣልያኑ ሴሪ ኤ ማሻሻጥ።

በታዳጊነታቸው በራዮላ ደላይነት ወደ ጣልያን ብሎም ወደ እንግሊዝ ገብተው ስማቸውን በጉልህ መፃፍ ከቻሉ ተጫዋቾች መካከል ዴኒስ ቤርግካምፕ የሚጠቀስ ነው።

ምንም ቢሆን የራሥ የራሥ ነው ያለው ራዮላ ተቀጥሮ ይሠራበት የነበረበትን ድርጅት ለቆ የራሱን የውክልና ድርጅት ሊያቋቁም ቻለ።

አሁን ላይ አውሮፓ ውስጥ ከሚጫወቱ እግር ኳሰኞች ስም ያላቸው በርካታ ተጨዋቾች ውክልናቸውን ለሚኖ ሰጥተው ነበር።

እንደ አውሮፓዊያኑ 2016 ላይ ራዮላ 'ታሪክ ሠራ'። ያኔ የዓለም ሬከርድ በነበረ ዋጋ ፖል ፖግባን ከዩቬንቱስ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ እንዲዛወር አደረገ፤ ዋጋው ደግሞ 105 ሚሊዮን ዩሮ።

ጉደኛው ራዮላ ከዚህ ዝውውር 25 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ወደ ኪሱ እንዳስገባ ይነገራል።

ከዚያ በኋላ ወደ አሜሪካዋ የባህር ዳርቻ ግዛት ማያሚ አቅንቶ 9 ሚሊዮን ዩሮ ማፍሰስ ቤተ-መንግሥት የሚያስንቅ መኖሪያ 'መንደር' ሸመተ።

ሚኖ ከፈጸማቸው ውድ የተጫዋቾች ዝውውሮች መካከል

  • ፖል ፖግባ እአአ 2016 ላይ ከጣሊያኑ ጁቬንቱስ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ በ89 ሚሊዮን ፓዎንድ
  • ሮሜሉ ሉካኩ እአአ 2017 ላይ ከኤቨርተን ወደ ማንችስተር ዩናይትድ በ75 ሚሊዮን ፓዎንድ
  • ማቲያስ ዲ ላይት እአአ 2019 ላይ ከአያክስ ወደ ጁቬንቱስ በ67.5 ሚሊዮን ፓዎንድ

ፎርብስ እአአ 2018 ላይ ባወጣው ዘገባ ሚኖ 69 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ገቢ ያለው ሲሆን በእርሱ ውክልና ሥራ ያሉ 70 ተጫዋቾች 629 ሚሊዮን ዶላር ሊያወጡ ይችላሉ ሲል አትቷል።

ሰውየው ያሻውን ከመናገር ወደኋላ የሚልም አይደለም። በአትንኩኝ ባይነቱ የሚታወቀው ራዮላ በእርሱ ውክልና ሥር ያሉ ተጨዋቾችን የሚተቹ የቀድሞ እግር ኳሰኞችም ሆነ ተንታኞችን በመወረፍ ይታወቃል።