ልቅ የወሲብ ፊልም ምክር ቤት ውስጥ የተመለከቱ እንደራሴ ከአባልነት ተገለሉ

ኒል ፔሪሽ

የፎቶው ባለመብት, UK Gov

በዩይናትድ ኪንግደም ምክር ቤት የሕዝብ እንደራሴ የሆኑት ኔል ፓሪሽ በምክር ቤት ሆነው በስልካቸው ልቅ የወሲብ ፊልም ሲመለከቱ ተይዘዋል፡፡

የተከበሩ ኒል ፓሪሽ በድርጊታቸው ክፉኛ መጸጸታቸውን ለቢቢሲ ከተናገሩ በኋላ በገዛ ፈቃዳቸው ከሕዝብ እንደራሴነት ለቀዋል፡፡

የተከበሩት የምክር ቤት አባል በቢቢሲ ቲሌቪዥን ቀርበው፣ ‹እብደታዊ ቅጽበት ነበር፤ምን እንደነካኝ አላውቅም፡፡› ብለዋል፡፡

እንደራሴ ፓሪሽ የቲቨርተን እና ሆኒቶን ዙርያ፣ ዴቮን የምርጫ ጣቢያ የሕዝብ ተመራጭ ነበሩ፡፡

ይበልጥ አነጋጋሪ የሆነው ሰውየው የወሲብ ፊልም የተመለከቱት አንድ ጊዜ ብቻ አለመሆኑ ነው፡፡

እሳቸውም እንዳመኑት መጀመርያ ሌላ አንድ የቁም ነገር ድረ-ገጽ እያሰሱ ሳለ በስም መመሳሰል ሊሆን ይችላል በስህተት የወሲብ ፊልም የያዘ ገጽ መጣባቸው፡፡

በኋላ ግን ነገሩን ደገሙት፡፡ በሌላ ጊዜ በታችኛው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ሳሉ ሥራዬ ብለው የወሲብ ፊልም ሲመለከቱ ነበር፡፡

ዓርብ ዕለት ሰውየው ከኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ አባልነት ወዲያውኑ የታገዱ ሲሆን ይህም የሆነው ሁለት ሴት የምክር ቤት አባላት ሰውየውን ከዚህ ቀደምም የወሲብ ፊልም ሲመለከቱ ተመልክተናቸዋል ብለው ምስክርነት መስጠታቸውን ተከትሎ ነው፡፡

"የፈጸምኩት እጅግ ጸያፍና ወራዳ ተግባር ነው፡፡ ያሳዝናል፤ ይህ ውርደት ሕይወቴን ሙሉ ይከተለኛል፡፡" ሲሉ እንባ እየተናነቃቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡

የተከበሩ ሚስተር ፓሪሽ ለ12 ዓመታት የምክር ቤት እንደራሴ ሆነው የቆዩ አንጋፋ ፖለቲከኛ ነበሩ፡፡

በሌላ በኩል ከታይም መጽሔት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የሚስተር ፓሪሽ ባለቤት ክፉኛ እየተብጠለጠሉ ያሉትን ባላቸውን ተከላክለዋል፡፡

"ተወዳጅ ባል ነው፤ ጤናማ ሰው ነው፡፡ የወሲብ ፊልም በሚያዩ ባሎች ሁሉ የምንበሳጭ ከሆነ በዚህ ምድር ላይ ብዙ ሚስቶች አይኖሩም ነበር፡፡" ሲሉ ድርጊቱ ያን ያህልም መጋነን እንደሌለበት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡