የጊኒ ወታደራዊ አስተዳደር ሥልጣን ለሲቪል አስተዳደር አስረክባለሁ አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጊኒ ወታደራዊ መንግሥት ከ39 ወራት የሽግግር ጊዜ በኋላ ሥልጣን ለሲቪል አስተዳደር አስረክባለሁ አለ፡፡
የጁንታው አለቃ ኮሎኔል ማማዲ ዱምቦያ በቴሌቪዥን ቀርቦ ይህ ጊኒን በ3 ዓመታት ወደ ሲቪል አስተዳደር የማሸጋገሩ ምክረ ሐሳብ ለጊኒ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይጸድቃል፡፡
ወታደራዊው ኃይል ባለፈው ዓመት የአገሪቱን ተመራጭ ፕሬዝዳንት በመፈንቅለ መንግሥት ካስወገደ በኋላ አገሪቱን በመምራት ላይ ይገኛል፡፡
በርካታ ጊኒያዊያን ይህን መፈንቅለ መንግሥት ደግፈውት ነበር፡፡
ሆኖም ግን እየቆየ ሲሄድ ወታደሮቹ ሥልጣን ለሲቪል አስተዳደር እንዲያስረክቡ ከሕዝብ ጫና በርትቶባቸዋል፡፡
ይህ የወታደራዊው አገዛዝ መግለጫ የመጣው የምዕራብ አፍሪካ አገራት ኅብረት የሆነው ኢኮዋስ ወታደራዊው መንግሥት እስከ ሰኞ ዕለት ወደ ሲቪል አስተዳደር የሚመለስበትን ዕቅድ ካላቀረበ ማዕቀብ እንደሚጥሉ ከዛቱ በኋላ ነው፡፡
መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ 80 አባላት ያሉት የጊኒ የሽግግር ምክር ቤት ተመሥርቷል፡፡ ይህ ካውንስል ነው አሁን የጊዜ የተወካዮች ምክር ቤት ሥራን የሚሠራው፡፡
የሦስት ዓመት ከሦስት ወራት የሽግግር ጊዜ እንዲኖር ምክረ ሐሳብ የቀረበው ለዚህ ካውንስል ነው፡፡
ኮሎኔል ዳምቦያ እንዳለው እሱን ጨምሮ ማንም ቢሆን በዚህ የሽግግር መንግሥት ጣልቃ መግባት አይችልም፡፡
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት መስከረም ላይ ነበር ይህ ወታደራዊ ጁንታ የ84 ዓመቱን ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴን በንቅዘት እና ሙስና በመክሰስ ከመንበራቸው ያስወገዳቸው፡፡
ፕሬዝዳንቱ በተለይም ለሦስተኛ ዘመን በሥልጣን ለመቆየት ሲሉ የሕግ መንግሥት ማሻሻያ ካደረጉ ወዲህ በሕዝብ ዘንድ የነበራቸው ተቀባይነት ወድቋል፡፡
በርካታ ጊኒያዊያን መፈንቅለ መንግሥቱን አዲስ ተስፋ አድርገው ተመልክተውት የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ለውጡ አዝጋሚ ሆኖባቸዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምዕራብ አፍሪካ መፈንቅለ መንግሥት ተበራክቶ ታይቷል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ የማሊና የኒጀር ይገኝበታል፡፡












