ሰላም አስከባሪ የትግራይ ተወላጆች ወደ ኢትዮጵያ አንመለስም ያሉት በህወሓት ፕሮፖጋንዳ 'ተታልለው' እንደሆነ መከላከያ ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአገር መከላከያ ሚኒስቴር በሱዳን ተሰማርተው የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የሰላም አስከባሪ አባላት ወደ ኢትዮጵያ አንመሰስም ያሉት በህወሓት ፕሮፖጋንዳ 'ተታልለው' ነው አለ።
ሚኒስቴሩ ዛሬ ሚያዚያ 19/2014 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ "ህወሓት የትግርኛ ተናጋሪዎች ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ በውጭ በሚገኙ የወያኔ ቅጥረኞች የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛቱ በአባላቱ ላይ ውዥንብር ፈጥሯል" ብሏል።
መከላከያ ይህን ያለው በመቶዎች የሚቆጠሩ እና በሱዳን አቢዬ ተሰማርተው የነበሩ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ የተመድ የላም አስከባሪ ኃይል አባላት ወደ ኢትዮጵያ አንመለስም ማለታቸው ከተዘገበ በኋላ ነው።
እንደ ዘገባው ከሆነ ሰላም አስከባሪዎቹ ለመመለስ ፍቃደኛ ያልሆኑት ለደህንነታቸው በመስጋት ነው።
እነዚህ ሰላም አስከባሪዎች ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ትገባኛለች በሚሏት የአብዬ ግዛት ተሰማርተው የነበሩ ናቸው።
የአገር መከላከያ ሚኒስቴር በዛሬው መግለጫ፤ "አገር ቤት ከተመለሳችሁ ትታሰራላችሁ የሚል የማስፈራሪያ ውሸት በመንዛትና ዘረኝነት በመቀስቀስ አገራቸውንና ተቋማቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የሠራዊት አባላትን የማስኮብለል ስራ ተሰርቷል" ብሏል።
በተፈጥሮ ሀብት በታደለችው የአቢዬ ግዛት የመንግሥታቱ ድርጅት ካሰማራቸው ሰላም አስከባሪዎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የኢትዮጵያ ሠራዊት ነው።
በዚህ ኃይል ውስጥ በአጠቃላይ ከተለያዩ አገራት የተወጣጡ 4 ሺህ 190 ሰላም አስከባሪዎች የተካተቱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም 3 ሺህ 158 ወታደሮችና ሰባት የፖሊስ መኮንኖች ከኢትዮጵያ መሆናቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
አምና በሱዳን ዳርፉር ውስጥ የተሰማራ ሌላ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ቡድን አባላትም ኢትዮጵያ ብንመለስ እንግልት ይደርስብናል በሚል ስጋት ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆኑም።
መከላከያ ሚኒስቴር በአሁኑ ወቅት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ያሉ እና "ለጊዜው ከስራ ውጭ" ሆነው ነገር ግን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅማቸው ተጠብቆ ያሉ የሠራዊት አባላት በህወሓት "አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ሳትንበረከኩ አገራችሁን አገልግሉ" ሲል ማሳሰቢያ ሰጥቷል።












