የዩክሬን ግጭት፡ ሩሲያ በዩክሬን የሚኮሊዬቭ የጦር ሰፈር ላይ በሰነዘረችው ጥቃት ብዙዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተነገረ

አርብ ዕለት በዩክሬን ወታደራዊ ሰፈር ላይ በደረሰ ጥቃት በርካታ የአገሪቱ ወታደሮች ተገድለዋል ተብሎ ተሰግቷል።
በሰሜናዊ ሚኮሊዬቭ ውስጥ የሚገኘው የጦር ሰፈር በሦስት የሩሲያ ሚሳኤሎች ሲመታ 200 የሚጠጉ ወታደሮች በጦር ሰፈሩ እንደነበር አንድ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ጉዳት የደረሰባቸው 57 ሰዎች በሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ሌላ ምንጭ ገልጿል።
እስካሁን በሟቾች ቁጥር ዙሪያ ምንም ይፋዊ መረጃ አልተሰጠም።
ጥቃቱ ከተፈጸመ ከ30 ሰዓታት በኋላ የነፍስ አድን ሠራተኞች በግዙፍ የፍርስራሽ ክምር ስር አንድ ሰው አግኝተዋል ።
ግለሰቡን ከፍርስራሹ ክምር ላይ በቃሬዛ ተሸክመው ወደ አምቡላንስ በማስገባት ወደ መሃል ከተማ ተወሰዷል።
ቅዳሜ ምሽት በሚኮሊዬቭ ያለው የአየር ሁኔታ እጅግ ቀዝቃዛ በመሆኑ በሕይወት ያሉ ሰዎችን ማግኘት ከባድ ሊሆን ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
የክልሉ ኃላፊ ቪታሊ ኪም እንዳሉት ሩሲያውያንን "በፈሪ እርምጃ የተኙ ወታደሮችን በሮኬት መተዋል" ሲሉ ወቅሰዋል።
ማክስም የተባለ ወታደር ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል "ቢያንስ 50 አስከሬኖች ተገኝተዋል። ምን ያህሉ በፍርስራሹ ውስጥ እንዳሉ ግን አናውቅም" ብሏል።
ነፍስ የማዳን ሥራው እየተከናወነ ያለውም አዲስ የሩሲያ ጥቃቶች ይኖራሉ በሚል ስጋት ውስጥ ነው።
ጥቃት በተፈጸመበት ስፍኣረ የተሰማራ ክሬን የኮንክሪት ፍርስራሾችን እና ብረትን እየጎተተ እያለ አካባቢውን የሚጠብቁ ወታደሮች የአውሮፕላን ወይም የሚሳኤል ድምፅ ስለሚሰማ ጋዜጠኞች እንዲሸሸጉ አዘው ነበር።
ከሰከንዶች በኋላ በሰሜን-ምሥራቅ በኩል አስፈሪ ፍንዳታ ተሰማ።
በተፈጸመው ጥቃት ከጦር ኃይሉ አቅራቢያ አንድ ሱቅ ደጃፍ የተሰለፉ ዘጠኝ ንፁሃን ዜጎችን ተገድለዋል። ቢቢሲ በቦታው ያገኛት ዩሊያን ስለ አጋጣሚው ስትናገር በእንባ ተሞልታ ነበር።
"ምን ያህል እንደፈራን ልነግርህ አልችልም። ሁላችንም የምንኖረው በጉድጓድ ውስጥ ነው። የጦሩ ሰፈር ሲመታ ሁሉም ነገር ተንቀጠቀጠ" ብላለች።
በቅርብ ርቀት የሚኖረው አንድሬ አንሲሞቭ ከሌላ የሩሲያ ጥቃት ለማምለጥ እየሞከረ ነው። በጥቃቱ የተፈጠረው ጉድጓድ በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ መኪና እና ቤት ውስጡ ወድቀዋል።
በጥቃቱ ወቅት አንድሬ እና ቤተሰቡ በአጋጣሚ በአካባቢው አልነበሩም።
"ይህ በወታደሮች መካከል የሚደረግ ጦርነት አይደለም። ሩሲያውያን ሁላችንንም ለማጥፋት እየሞከሩ ነው" ብሏል።
ሩሲያ በጥቁር ባሕር ዳርቻ በኩል ወደ ምዕራብ የምታደርገውን ጉዞ ሚኮሊዬቭ ለሳምንታት ስታግድ ቆይታለች። ይሁን እንጂ በአንድ ሌሊት በከተማዋ በስተደቡብ አቅጣጫ ከባድ ጥቃት ተፈጸመ።
ወታደራዊ ዒላማዎችን ለማግኘት የተላኩ የሩሲያ የስለላ ቡድኖች በዚያ መገኘታቸውንም ዘገባዎች አመልክተዋል።












