አሜሪካ ለዩክሬን የሰጠቻቸው የጦር መሣሪያዎች የኃይል ሚዛን ለውጥ ያመጡ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድ የሩሲያ ታንክ ዶግ አመድ ሆኖ አፅሙ መንገድ ዳር ተጋድሟል። ያን የሚያህል ታንክ ትከሻው ላይ በተሸከመው ዘመናዊ መሣሪያ የፈረካከሰው ዩክሬናዊ ወታደር በማናለብኝነት ደረቱን ነፍቶ ቆሟል።
ይህ ምስል በዩክሬን መከላከያ ሠራዊት የትዊተር ገፅ ላይ የተለጠፈ ነው።
ከምስሉ በታች የሚነበበው ፅሑፍ ጃቫሊን በተሰኘው የ21ኛው ክፍለ ዘመን የጦር መሣሪያ ብትንትኑ የወጣ ታንክ እንደሆነ ይጠቅሳል።
ጃቫሊን ትከሻ ላይ የሚሸከሙት ፀረ-ታንክ መሣሪያ ነው። እስከ 4 ኪሎ ሜትር ይመዘገዘጋል።
መሣሪያውን ልክ እንደሕፃናት የኮምፒውተር ጨዋታ መቆጣጠሪያ ባለች እጀታ ማዘዝ ይቻላል። ይህ መሣሪያ የሚተኩሰው ቅንቡላ ግን ብረት ለበስ ተሽከራካሪዎችን ከምድረ-ገጽ የሚጠራርግ ነው።
"አሜሪካ ሠራሽ መሣሪያዎችን መታጠቃችን ሩሲያዊያን ያስበረግጋል" - ይላል 2 ሺህ ጃቫሊን የታጠቀው የዩክሬን ጦር።
አሜሪካ ለዩክሬን 800 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታለች። ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ናቸው ረቡዕ ዕለት 'ዩክሬን ሆይ ብረሳሽ. . .' ሲሉ ቃል የገቡት።
ጃቫሊንን ጨምሮ ከሰማይ ቁልቁል እየተመለከተ ቦምብ የሚተፋ፤ ከሄሊኮፕተሮች ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ የሚተኩስ ሰው አልባ አውሮፕላን [ድሮን] እንዲሁም ድሮን ላይ የሚጠመዱ መሣሪያዎች ናቸው ከአሜሪካ የሚቀርቡት።
ነገር ግን ጥያቄው ወዲህ ነው። እውን እኒህ መሣሪያዎች ዩክሬን እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የሩሲያ ጦር እንድትገታ ያስችላታል?
መጀመሪያ የአሜሪካን ልገሳ በዝርዝር እንመልከት።
ባይደን 25 ሺህ የሰውነት መከላከያ እና ሄልሜት [ጭንቅላት መሸፈኛ ቆብ] ለዩክሬን ወታደሮች ለማደል ቃል ገብተዋል።
ይህ ብቻ አይደለም ቀላል መሣሪያን ጨምሮ ቦንብ ወርዋሪ መሣሪያዎችን እንዲሁም በርካታ ሺህ ታንክ መቋቋሚያ ማሽኖችን እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠር ጥይቶች ለዩክሬን ይበረከታል።
እጅግ ዘመናዊና ጨዋታ ቀያሪ ከሚባሉት ተርታ ደግሞ ጃቫሊን ሚሳዔል እና ስቲንገር ፀረ-አውሮፕላን መሣሪያ ይገኙበታል።

ዩናይትድ ስቴትስ ልገሳውን በዚህ አልገታችም። 100 ለአየር ቅኝት የሚያገልግሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖች [ድሮኖች] ለዩክሬን ለማስታጠቅ አስባለች።
ረቡዕ ዕለት ጆ ባይደን ለዩክሬና ቃል የገቡትን ወታደራዎ ልገሳን ጨምሮ አሜሪካ ለዜሌንስኪ አገር 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ እርዳታ አድርገዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ በፈረንጆቹ ከ2014 እስከ 2021 መጨረሻ ባለው ጊዜ ለዩክሬን ያደረገችው እርዳታ ተደማምሮ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ነበር።
እነሆ ከሩሲያ ወረራ በኋላ ባሉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ ግን ዩክሬን ከአሜሪካ የ1 ቢሊዮን ዶላር ድጎማ በወታደራዊ መሣሪዎች መልክ ተቀብላለች።
"ይህ ትልቅ ለውጥ ነው" ይላሉ በኪዬቭ የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ጆን ኸርብስት።
የአሜሪካ እርዳታ ለውጥ ያመጣ ይሆን?
የወታራዊ ሳይንስ አዋቂዎች አሜሪካ ሠራሽ የጦር መሣሪያዎች ዩክሬን ውስጥ ባለው ጦርነት የሚዛን ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ይላሉ።
ዩክሬን ውስጥ ያለው የሩሲያ ጦር በዋናነት 'ሜካናይዝድ ነው'። ይህ ማለት ብረት ለበስ ተሽከርካሪ ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው ይላሉ የቀድሞው የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል አባል ኮሎኔል ክርስቶፈር ሜየር።
"ይህን መሰል ጦር ማጥቃት የምትችለው ተሽከርካሪውን በመምታት ነው" ይላሉ ኮሎኔሉ።
"ዩክሬን ታንክ መቋቋሚያ ካገኘች የትኛውንም ዓይነት እግረኛ ጦር እየፈረካከሰች ልታልፍ ትችላለች።"
ምንም እንኳ ይህን መረጃ ማጣራት ባይቻልም የዩክሬን ባለሥልጣናት በልገሳ የተሰጧቸውን የጦር መሣሪያዎች ጥቅም ላይ እያዋሉ እንደሆነ ይናገራሉ።
የዩክሬን ባለሥልጣናት ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ 400 ታንኮች እና 2 ሺህ የሩሲያ ተሽከርካሪዎችን ከጥቅም ውጭ አድርገናል ይላሉ።
ነገር ግን ላለፉት ሦስት ሳምንታት ዒላማ እየመረጡ ለሚያወድመው የሩሲያ አየር ኃይል የታንክ መቋቋሚያ ማለት ምንም አይደለም።
ከሰው ትከሻ ላይ ተወንጭፎ በሰማይ በራሪ ጦረኞችን የሚለቅመው ስቲንገር ብቻ ነው የሩሲያን የደመና ሠራዊት ሊቋቋም የሚችለው።
ይህ ስቲንገር የተሰኘው የጦር መሣሪያ ከፈረንጆቹ 1981 ጀምሮ በተለያዩ የጦር አውድማዎች ላይ ታይቷል።
ሶቪዬት ሕብረት አፍጋኒስታንን በወረረች ጊዜ አሜሪካ ሠራሹ ስቲንገር የሩሲያን ግዙፍ የጦር አውሮፕላን በመብረቅ ፍጥት እንደበታተነው ይነገራል።
ነገር ግን ይህ መሣሪያ ውጤታማ የሚሆነው ዝቅ ብለው ከ12 ሺህ ጫማ ባልበጠ ከፍታ ላይ ለሚበሩ የጦር አውሮፕላኖች እንጂ ከዓይን ርቀው ለሚጠቁት የሩሲያ ጄቶች አይደለም።
ኮሎኔሉ የባይደን አስተዳደር ስቲንገርን እንደ ትልቅ ስጦት ተመልክቶ ማወጁ "የሽንፈት ምልክት ነው" ይላሉ።
"ስቲንገር እንደሚያስፈልጋቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ከከፍታ ላይ ነጥለው የሚጥሉ መሣሪያዎችም ያስፈልጋሉ።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩክሬን ከአሜሪካ የቀረባት ምንድነው?
ምንም እንኳ ዋይት ሐውስ ኤስ-300 የተሰኘው ፀረ-የጦር አውሮፕላን ማሽን ወደ ዩክሬን ሊላክ እንደሚችል ቢጠቁምም ይፋዊ መግለጫ ከመስጠት ግን ተቆጥቧል።
የስሎቫኪያ ባለሥልጣናት ምትክ የጦር መሣሪያ የሚሰጣቸው ከሆነ በእጃቸው ያለውን ለዩክሬን ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ሌሎች ሁለት የኔቶ አባላት - ግሪክና ቡልጋሪያም ይህ የጦር መሣሪያ እንዳላቸው ይነገራል።
ፖላንድ ያሏትን ሚግ-29 ተዋጊ ጄት ለዩክሬን ልትሰጥ ይሆን ተብለው የተጠየቁት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጉዳዩን አድበስብሰው አልፈውታል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ይህ ዕቅድ 'ተፈፃሚ አይደለም'፤ አልፎም በኔቶና በሩሲያ መካከል ያለውን ግንኙነት ሊያባብሰው ይችላል።
ኮሎኔል ሜየር እንደሚሉት አሜሪካ ሚግ-29 አሊያም ተመሳሳይ ጄቶችን ለዩክሬን ብትለግስ የዜሌንስኪ ጦር የፑቲንን የአየር ላይ ታላቅነት ሊቋቋመው ይችላል።
ሌሎች አገራትስ ምን አበረከቱ?
ለዩክሬን ወታደራዊ እርዳታ ያደረገችው አሜሪካ ብቻ አይደለችም። ቢያንስ ሌሎች 30 አገራት እጃቸውን ዘርግተዋል። ከእነዚህ መካከል የአውሮፓ ሕብረት ያደረገው የ500 ሚሊዮን ዩሮ እርዳታ የሚጠቀስ ነው።
አሜሪካ ለዩክሬን እርዳታ ለማድረግ ቃል ከገባች በኋላ ዜሌንስኪ "ተጨማሪ እርዳታ" እንደሚያሻቸው ተናግረዋል።
"አሁን ከተሰጠን በላይ ያስፈልገናል" ሲሉ በግልፅ ዩክሬንኛ ለዓለም መሪዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
"የጦር አውሮፕላን መቋቋሚያ ያስፈልገናል፤ በቂ የጦር መሣሪያና ጥይት ያስፈልገናል፤ የሩሲያን ጦር ለመቋቋም ይህ ያስፈልገናል።"
ኮሎኔል ሜየር እስካሁን አሜሪካ ለዩክሬን የለገሰቻቸው መሣሪያዎች ዩክሬናዊያን "ተጋድለው እንዲሞቱ" የሚያደርጉ እንጂ በቂ አይደሉም ይላሉ።
ምንም እንኳ አሜሪካ በይፋ ከማወጅ ብትቆጠብም ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ተጨማሪ እርዳታ ወደ ዩክሬን ይላካል ሲሉ ተደምጠዋል።

ስለጦርነቱ ተጨማሪ ዘገባዎች













