ኤርትራ ውስጥ በርካታ የወንጌል አማኞች መታሰራቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤርትራ ውስጥ በርካታ የወንጌላውያን ቤተክርስቲያን አማኞች በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው መታሰራቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።
በአጠቃላይ 29 እንደሆኑ የተነገረላቸው የወንጌላዊ ቤተክርስቲያን ምዕመናኑ በዋና ከተማዋ አሥመራ ከተማ ውስጥ ከሚገኝ ቤተ እምነት ውስጥ ነው ተይዘው ወደ እስር ቤት የተወሰዱት።
ከቀናት በኤርትራ መንግሥት የፀጥታ አባላት ተይዘው ለእስር ከተዳረጉት ሰዎች መካከል 12ቱ ወንዶች እና 17ቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ክርስቲያን ምዕመናኑ በአሁኑ ጊዜ ማይስርዋ ተብሎ በሚታወቀው እስር ቤት ውስጥ ለቀናት ታስረው እንደሚገኙ ምንጮቹ ለቢቢሲ ጨምረው አስረድተዋል።
ይህ ማይስርዋ በመባል የሚታወቀው እስር ቤት በታሳሪዎች ላይ አካላዊ ስቃይን ጨምሮ ሌሎችም አስከፊ የመብት ጥሰቶች ከሚፈጸምባቸው እስር ቤቶች አንዱ እንደሆነ ከዚህ በፊት በእስር ቤቱ ታስረው የነበሩ ሰዎች ይናገራሉ።
የኤርትራ መንግሥት የወንጌላውያን ቤተክርስቲያንን ጨምሮ በአንዳንድ የእምነት ተቋማትና ተከታዮቻቸው ላይ ያተኮረ ጫናን እንደሚያሳድር በአሜሪካና በመብት ተቋማት ሲከሰስ ቆይቷል።
ከአስር ዓመት በፊት በአውሮፓውያኑ 2002 ላይ በርካታ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን በመዝጋት የእምነት መሪዎችና አማኞች ላይ የመብት ጥሰት መፈጸሙንና በርካቶች ለእስር መዳረጋቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች መውጣታቸው ይታወሳል።
ነገር ግን ከወራት በፊት በአገሪቱ ውስጥ በእስር ላይ የነበሩ በርካታ የወንጌላውያን ቤተክርስቲያን አማኞች ከእስር እንዲፈቱ በመደረጉ የሚደርስባቸው ጫና ይቃለላል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
ባለፈው የካቲት ወር ለዓመታት በቤታቸው ውስጥ በቁም እስር ላይ የቆዩት የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሦስተኛው ፓትሪያርክ የነበሩት አቡነ አንጦንዮስ በቁም እስር ላይ ሳሉ በ94 ዓመታቸው ማረፋቸው ይታወሳል።
በቅርብ ጊዜያትም የኤርትራ መንግሥት በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚያደርገውን ጫና በመቀጠል በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሥር ይተዳደሩ የነበሩ የጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶችን በራሱ ቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል።
የኤርትራ ባለሥልጣናት በዚህ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ክስ ሲቀርብባቸው፤ ክሶቹ የኤርትራን ስም ለማጠልሸት በምዕራባውያን መንግሥታት የተቀናበሩ ውንጀላዎች ናቸው በማለት ውድቅ ሲያደርጉት ቆይተዋል።
ባለፉት ዓመታት የመብት ተቋማት የኤርትራ መንግሥት በዜጎች የእምነት ነጻነት ውስጥ ተጽእኖ እንሚያሳድርና የተለያዩ እርምጃዎችን እንደሚወስድ በሚያወጧቸው ሪፖርቶች ሲተቹ ነበር።
ኤርትራ ከእምነት ነጻነት ባሻገር በተለያዩ የመብት ጥሰቶች ስትከሰስ ቆይታለች።
በተባሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ከሳምንት በፊት ባወጣው ሪፖርት፤ በኤርትራ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ መሻሻል እንዳልታየ አሳውቆ ነበር።
በተባበሩት መንግሥታት የኤርትራ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ልዩ ልዑክ መሐመድ አብደይሰላም ባቢካ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ "በአገሪቱ የሰብአዊ አያያዝ መሻሻል ስለመኖሩ የሚያሳይ ምልክት አላገኘንም" ብለዋል።
አክለውም "የተቃውሞ ድምጽ በሚያሰሙ ላይ መንግሥታዊ አፈና እና መሰወር ቀጥሏል። የመናገር መብት፣ ሐሳብን የመግለጽ መብት፣ የመደራጀት መብት እንዲሁም የሃይማኖት ነጻነት መገደቡ አልቆመም። የሲቪልና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዝግ ሆነው ይገኛሉ" ብለዋል።












