ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል ለማዞር የተያዘው ዕቅድ እንዲዘገይ ተደረገ

የኢትዮጵያ መንግሥት ከጥቂት ዓመታት በፊት ይፋ ያደረገውን ምጣኔ ሀብታዊ ማሻሻያ ተከትሎ በአገሪቱ ብቸኛ የነበረውን መንግሥታዊ የቴሌኮም ተቋም በከፊል ወደ ግል ለማዞር የነበረውን ዕቅድ ወደ ሌላ ጊዜ አዘዋወረ።
በአገሪቱ መንግሥት በብቸኝነት ተይዘው የነበሩ ተቋማትን በከፊል ወደ ግል ለማዞር እና ሌሎች ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ለማስቻል ክፍት ከተደረጉት ዘርፎች መካከል ቴሌኮም አንዱ ነው።
በዚህም ከአንድ መቶ ዓመት በላይ በአገሪቱ በብቸኝነት የቴሌኮም አግልገሎት ሲሰጥ የቆየውን የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ በመሸጥ ሌሎችን ለማሳተፍ ጥሪ ቀርቦ በሂደት ላይ መሆኑ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ዛሬ አርብ መጋቢት 09/2014 ዓ.ም ይፋ እንዳደረገው መንግሥት የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ የባለቤትነት ድርሻን ወደ ግል ለማዞር እየተካሄደ የነበረውን ሂደት ወደ ሌላ ጊዜ ያተላለፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ በታዩ ፈጣን ማክሮኢኮኖሚያዊ ለውጦች ምክንያት ነው ብሏል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውስጥ ከተካተቱት ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ለግል ክፍት እንዲደረግ ቢወሰንም፣ ከፍተኛው የ60 በመቶው ድርሻ በመንግሥት እጅ የሚቆይ ይሆናል።
ይህ የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ በከፊል ፍላጎቱ ላላቸው ወደኖች ለማስተላለፍ የነበረው ሂደት እንዲዘገይ በመደረጉ በማክሮኢኮኖሚው ላይ መሻሻሎች እንዲታዩና የኢትዮ ቴሌኮም የገንዘብ አቅም እንዲያድግ በማድረግ ዋጋውን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል እምነቱን ገልጧል።
ነገር ግን መንግሥት በእቅዱ መሠረት የተጀመረውን ወደ ግል የማዘዋወር ሂደት በመቀጠል ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አመልክቶ አመልክቶ፣ እስካሁን የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመግዛት ፍላጎታቸውን ካሳዩትና በሂደቱ የተሳተፉትን እንዲሁም ሌሎችም ፍላጎቱ ያላቸውን ጨምሮ ሂደቱን እንደሚቀጥል ገልጿል።
በ110 ሚሊዮን ሕዝብ ከአፍሪካ በሕዝብ አገሪቱ ሁለተኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ በብቸኝነት የቴሌኮም አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ኢትዮ ቴሌኮም ከ52 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይታመናል።
ከአገሪቱ ሕዝብ ወደ ግምሽ ለሚጠጋውን የስልክ፣ የኢንተርኔትና ሌሎች የቴሌኮም አገልግሎትን እየሰጠ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም በአፍሪካ ውስጥ በዘርፉ ግዙፍ ከሚባሉት ተቋማት መካከል የሚጠቀስ ነው።
መንግሥት የቴሌኮም ዘርፉን ለሌሎች ተወዳዳሪዎች ክፍት ማድረጉን ተከትሎ በግዙፉ ሳፋሪኮም የሚመራው የተለያዩ ኩባንያዎች ጥምረት ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ እንዲጀምር ፈቃድ ማግኘቱ ይታወሳል።
ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ በኢትዮ ቴሌኮም ተይዞ የቆየው የአገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍን የተቀላቀለው ሳፋሪኮም ባለፉት ወራት አስፈላጊዎቹን መሠረተ ልማቶች በመዘርጋት በሚቀጥለው ወር ሥራውን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።
















