ኢትዮ ቴሌኮም ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ባለፉት 6 ወራት 3.67 ቢሊዮን ብር ማጣቱን አስታወቀ

ኢትዮ ቴሌኮም ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተያያዘ ባለፉት ስድስት ወራት 3.67 ቢሊዮን ብር ገቢ ማጣቱን አስታውቋል።
በዚህም ተቋሙ ይዞት የነበረው የገቢ ዕቅድ ሙሉ በሙሉ እንዳልተሳካና ባለፉት ስድስት ወራትም ይገኛል ተብሎ ከታቀደው ገቢ 86.4 በመቶ ብቻ ማሳካቱንም በ2014 ዓ.ም የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ማጠቃለያ ሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል።
ከሐምሌ 2013 እስከ ታኅሣሥ 2014 ያለውን የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት መሰረት ጦርነቱ በመራዘሙና ከትግራይ ክልል ወደ አፋርና አማራ ክልልሎች በመዛመቱ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 3473 የሞባይል ጣቢያዎች ላይ የአገልግሎት መስተጓጎል ተፈጥሯል ብሏል።
በጦርነቱ የተጎዱና እስካሁን መደረስ በተቻለባቸው አካባቢዎች ላይ አገልግሎቱን ለማስጀምር 328.9 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉንም ኢትዮ-ቴሌኮም ገልጿል።
ጦርነቱ ከተከሰተበት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የለም።
ኢትዮ-ቴሌኮም በሪፖርቱም ላይ ትግራይ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ ወረዳዎች በፀጥታ ምክንያት አገልግሎት መስጠት እንዳልተቻለና በስፍራው ያለው የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ እንዳልተቻለም አስፍሯል።
የፀጥታው ሁኔታ ሲሻሻልም አስፈላጊው የጥገናና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እንደሚከናወንም አስታውቋል።
ተቋሙ በመንፈቅ ዓመት 28 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ያገኘ ሲሆን ይሄም ባለፈው በጀት ዓመት ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ6.7 እድገት አሳይቷል ብሏል።
ይህ ውጤት አገሪቱ ከነበረችበት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ አንፃር ሲታይ አመርቂ መሆኑንም ነው ኢትዮ ቴሌኮም የገለጸው።
ኢትዮቴሌኮም የተጠቃሚ ደንበኞቹ ብዛት 60.8 ሚሊዮን መድረሱን ያስታወቀ ሲሆን እቅዱንም በከፍተኛ ሁኔታ ማሳካቱን አስታውቋል።
ደንበኞች የቴሌኮምን አጠቃቀምን ለማሳደግና ተሞክሯቸውን ለማሻሻል የሚያስችሉ የኔትወርክ ማስፋፊያዎች፣ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ፣ ወቅታዊነትን የተላበሱ 23 አዳዲስ እና 19 ነባር የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን አሻሸሎ ማቅረቡን ገልጿል።
ተቋሙ የኔትወርክ ሽፋን አቅም እና የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አጠቃላይ ሰፊ የፕሮጀክት ሥራዎች በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሶ በመንፈቀ ዓመቱም የ4ጂ ኤልቲኢ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ 136 ከተሞችንም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አድርጌያለሁ ብሏል።
በተጨማሪም የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የሆነው ቴሌ ብር በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ13 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያፈራ ሲሆን፣ አጠቃላይ የግብይት መጠኑም 5.1 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል። እስካሁንም ባለው 46 ሺህ በላይ ኤጀንቶችና ከ11 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ተሳታፊ መሆናቸውም ተገልጿል።
ሆኖም በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮች መግጠማቸውን ጠቅሷል።
ከእነዚህም መከካል የአገልግሎት መቋረጥና የመሠረተ ልማት መውደም፣ በታቀደው መሠረት የማስፋፊያ ሥራዎች ለመሥራትና አገልግሎት ማስቀጠል አዳጋች መሆን፣ የፋይበርና የኮፐር መስመሮች ስርቆትና መቆራረጥ፣ የቴሌኮም ማጭበርበር፣ የኃይል አቅርቦት መዘግየት እና የኃይል መቆራረጥን ጠቅሷል።
በተጨማሪም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ ለቴሌኮም ማስፋፊያ የመሬት አቅርቦት ችግር፣ አንዳንድ ክልሎች ላይ ተገቢ ያልሆነ የካሳ ጥያቄና ከዚሁ ጋር በተገናኘ የኩባንያው የባንክ ሂሳብ የማገድ ተግባራት መግጠሙንም አስታውቋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ለበርካታ ዘመናት በኢትዮጵያ ውስጥ በብቸኝነት የቴሌኮም አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ተቋም ሲሆን፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት መንግሥት ዘርፉን ለውድድር ክፍት በማድረጉ ሳፋሪኮም የተባለው የውጪ ኩባንያ በሥራው ላይ ለመሰማራት ፈቃድ አግንቷል።












