ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ እዘረጋዋለሁ ያለው 5ጂ ኢንተርኔት ምንድነው?

5ጂ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በእንግሊዝኛው አጠራር ፊፍዝ ጄኔሬሽን ወይም አምስተኛው ትውልድ የተንቀሳቃሽ ስልክ በይነ መረብ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ እንደሆነ የአገሪቱ ኔትዎርክ አቅራቢ ደርጅት ገልጿል።

ኢትዮ ቴሌኮም 4ጂ ማስፋፋቱን ሲያጠናቅቅ ወደ ለአገሪቱ የመጀመሪያው የሆነውን 5ጂ ሊያቀና መሆኑን ያሳወቀው በቅርቡ ነው።

ኢትዮጵያ 5ጂ ኢንተርኔትን ወደ አገር ቤት ለማስገባት ያሰበችው ከግዙፉ የቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሁዋዌ ጋር በመተባበር ነው።

በአፍሪካ በአሁኑ ወቅት 5ጂ ኢንተርኔትን እየተጠቀሙ ያሉ አገራት ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ብቻ ናቸው።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ይህን ዜና ይፋ ያደረጉት መሥሪያ ቤታቸው ለ52 ከተሞች 4ጂ ኢንተርኔት መዘርጋቱን ከገለጹ በኋላ ነው።

ለመሆኑ 5ጂ ምንድነው? ሕይወታችንን ሊቀይረው ይችል ይሆን? በየትኛው ስልክ እናገኘዋለን?

5ጂ እስካሁን ከምናውቃቸው ኢ፣ ኦ፣ ጂፒአርኤስ፣ እንዲሁም 3ጂ እና 4ጂ በፍጥነቱ ወደር የማይገኝለት ነው።

አምስተኛው ትውልድ [5ጂ] አሁን ፈጣን የሚባለውና ብዙዎች እየተጠቀሙበት ካለው የ4ጂ ኢንተርኔት በሃያ እጥፍ የፈጠነ ነው።

ይህም ማለት የትኛውንም ዳታ ወደ በይነ መረብ ለመጫንም ከበይነ መረብ ለማውረድ የሚፈጅብን ጊዜ ሃያ እጥፍ ያጠረ ይሆናል ማለት ነው።

ራድዮ ስፔክትረም የተሰኘውን ቴክኖሎጂ የሚጠቀመው 5ጂ በአንድ ጊዜ በርካታ ተንቃሳቃሽ ስልኮች በይነ መረብ እንዲያገኙ የማድረግ አቅም አለው።

"አሁን በስልኮቻችን የምንተገብራቸውን ነገሮች በተሻለ ፍጥነት መተግበር እንችላለን ማለት ነው" ይላሉ ኦፕንሲግናል የተሰኘው የሞባይል ዳታ ቀማሪ ድርጅት ባልደረባው ኢያን ፎግ።

ካሜራ አዝለው ምድርን ከሰማይ ሆነው የሚቃኙ ድሮኖች በዚህ ቴክኖሎጂ ታግዘው የእሣት አደጋ መኖር አለመኖሩን ሲመርምሩ፣ ትራፊክ ፖሊስን ሲያግዙ ያስቡት። ይህን እውን ለማድረግ ገመድ አልባው ፈጣኑ ቴክኖሎጂ 5ጂ ወሳኝ ነው።

5ጂ ሌላኛው ጥቅሙ አሽከርካሪ አልባ መኪናዎች እንደልባቸው እንዲቀሳቀሱ ያስችላል መባሉ ነው። እኒህ የመጪው ዘመን መኪናዎች ከሌሎች መሰል መኪናዎች እንዲሁም ከትራፊክ ሥርዓቱ ጋር ተሳልጠው እንዲሠሩ 5ጂን ይሻሉ።

የሞባይል ስልክ ጨዋታዎች ፈጣን ይሆናሉ። ተንቀሳቃሽ ምስሎችንም ያለምንም እንከን ይኮመኮማሉ። በተንቀሳቃሽ ምስል ከወዳጅ ዘመድዎ ጋር በነፃነት ያወራሉ. . . ሌላም ሌላም።

ይህ ቴክኖሎጂ የዓለም ኢኮኖሚ ኃያላኑን አሜሪካና ቻይና እስከ ማጋጨት ደርሷል። ለዚህም ደግሞ ምክንያት ረብጣ ዶላር ነው።

ይህን የቀጣዩ ዘመን ቴክኖሎጂ መቆጣጠር ማለት ለሚሊዮኖች የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲሁም በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገቢ ማግኘት ማለት ነው።

ኖሎጂው እንዴት ነው የሚሠራው?

ራድዮ ስፔክትረም የተሰኘ አዲስ ቴክኖሎጂን የሚጠቀመው 5ጂ መጀመሪያ ጥቅም ላይ የሚውለው በኔትዎርክ አቅራቢ ድርጅቶች ነው። ድርጅቶቹ ይህን የሚያደርጉት አሁን ከፍተኛ ፍጥነት ያለውን 4ጂ ኢንተርኔት ለማበልፀግ እንዲረዳቸው ነው።

የ5ጂ ፍጥነት እንደሚጠቀሙት ስፔክትረም እንዲሁም እንደ ሞባይል ኔትዎርክ አቅራቢዎች ይለያያል። ሞባይል ኔትዎርክ የሚያቀርብልዎ ድርጅት በርካታ ማስተላለፊያዎችን የመትከል አቅም ካለው የተሻለ ኢንተርኔት ይኖርዎታል ማለት ነው።

ነገር ግን ይህን ቴክኖሎጂ ለመዘርጋት የሚወጣው ወጪ ቀላል የሚባል ስላልሆነ ኔትዎርክ አቅራቢ ድርጅቶች ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችል እሙን ነው።

ሞባይል

የፎቶው ባለመብት, Thinkstock

ፍጥነቱ ምን ያክል ነው?

በአሁኑ ወቅት ብዙዎች በይነ መረብን የሚዘውሩበት 4ጂ ኢንተርኔት በአማካይ በሰከንድ 45 ሜጋባይት ዳታ ያሽከርክራል።

ነገር ግን 4ጂ በዚህ ብቻ ሳይገደብ በሰከንድ እስከ 1 ጂቢ [1 ሺህ ሜጋባይት] ኢንተርኔት ለማቅረብ አቅም እንዳለው ይነገራል።

5ጂ ይህንን የኢንተርኔት ፍጥነት ከ10 እስከ 10 እጥፍ ሊያደርሰው ይችላል። በሌላ ቋንቋ ኢንተርኔትን ለመዳሰስ አሊያም ፋይል ለማውረድ አሁን ከሚወስድብዎ ፍጥነት እስከ 20 እጥፍ ሊያድግ ይችላል ማለት ነው።

በዚህ ፍጥነት በከፍተኛ ጥራት የተሠራን አንድ ፊልም በአንድ ደቂቃ ከበይነ መረብ ሊያወርዱ ይችላሉ።

ይህ ፍጥነት እውን የሚሆነው ኔትዎርክ አቅራቢ ድርጅቶች የኮርና ራድዮ ኔትዎርኮች በ5ጂ ቴክኖሎጂ እንዲሠሩ ማድረግ ሲችሉ ነው።

5ጂ ለምን ያስፈልገናል?

ዓለማችን የተንቀሳቃሽ ቴክኖሎጂዎች ዓለም እየሆነች ነው። ሰዎች ከዓመት ዓመት የሚጠቀሙት ዳታም እያሻቀበ ነው።

በተለይ ደግሞ የተንቀሳቃሽ ምስሎች ተወዳጅነት እንዲሁም አዝናኝና መረጃ ሰጭ ዘገባዎች በቀጥታ መተላለፋቸው የተሻለ ኢንተርኔትን የሚጠይቁ ናቸው።

አሁን ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ የራድዮ ስፔክትረሞች እየተጨናነቁ ነው። በተለይ ደግሞ በርካታ ሰዎች በአንድ ቦታ በተመሳሳይ ሰዓት ኔትዎርክ ለማግኘት ሲጥሩ ቴክኖሎጂው ይጨናነቃል።

5ጂ፤ ተንቀሳቃሽ ቴክኖሎጂዎችን፣ የደኅንነት ካሜራዎችን እንዲሁም የመንገድ መብራቶች በአንድ ጊዜ በርካታ ሰዎች እንዲጠቀሙበት ያስችላል።

5ጂን ለመጠቀም አዲስ ስልክ ያስፈልገኝ ይሆን?

ሳያስፈልጎት አይቀርም። ነገር ግን 4ጂ በፈረንጆቹ 2009/10 ተግባራዊ ሲደረግ ይህንን ቴክኖሎጂ መሸከም የሚችሉ ስልኮች ወደ ገበያው ብቅ ብቅ ማለት ጀምረው ነበር።

አሁንም ይህን ቴክኖሎጂ መዘወር የሚችሉ ስልኮች በተመጣጣኝ ዋጋ ወደ ገበያው ሊመጡ ይችላሉ የሚል እምነት አለ።

ቴክኖሎጂ ገጠር ይደርሳል?

5ጂ ኢንተርኔት መጀመሪያ ጥቅም ላይ የሚያውሉት ኔትዎርክ አቅራቢ ድርጅቶች ናቸው። ለምሳሌ ኢትዮ-ቴሌኮም ቴክኖሎጂውን በዋና መሥሪያ ቤቱ አቅራቢያና እንደ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ባሉ ሥፍራዎች እንደሚያስጀምር ገልጿል።

5ጂ በፍጥነት ወደ ገጠር ይገባል ማለት ባይቻልም ጊዜ ጠብቆ መድረሱ አይቀርም።

ኢትዮጵያ እንደ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ይህን ቴክኖሎጂ ቀድመው ካስገቡ የአፍሪካ አገራት ተራ ለመመደብ ደፋ ቀና እያለች ነው።

በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ፈቃድ ያገኘው ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለው የስድስት ኩባንያዎች ጥምረት የሆነው ተቋም በ4ጂ ጀምሮ ወደ 5ጂ ለማደግ እንዳሰበም ታውቋል።