በሳዑዲ አረቢያ ለ30 የባቡር አሽከርካሪነት የሥራ ቅጥር 28 ሺህ ሴቶች አመለከቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሳዑዲ አረቢያ 30 ሴት የባቡር አሽከርካሪዎችን ለመቅጠር የሥራ ማስታወቂያ ያወጣው የባቡር ድርጅት ከ28 ሺህ ሴቶች ማመልከቻዎችን መቀበሉን ገለጸ።
በዚህ የሥራ ውድድር ያለፉ ተወዳዳሪዎች የአንድ ዓመት ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ በቅዱስ ከተሞቹ መካ እና መዲና መካከል ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸውን ባቡሮች ይነዳሉ።
በወግ አጥባቂው የሙስሊም ግዛት ለሴቶች እንዲህ ዓይነት የሥራ ማስታወቂያ ሲወጣ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ላለፉት አስርተ ዓመታት ሳዑዲ አረቢያ በዓለም ዝቅተኛ የሆነ የሴቶች ሠራተኛ ኃይል ተሳትፎ ያላት አገር ነበረች።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን መንግሥት በሥራ ላይ ያሉ ሴቶችን ቁጥር ለማሳደግ እየሰራ ሲሆን ይህ በነዳጅ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚን ለማስፋፋት ያለመው የልዑል መሀመድ ቢል ሰልማን እቅድ አካል ነው።
ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት ሴቶች እንዳያሽከረክሩ የጣለውን እገዳ ማንሳትንና ሴቶች በነጻነት ለመጓዝ ወንድ ጠባቂ ያስፈልጋቸዋል የሚለውን ሕግ ማላላትን ጨምሮ የተለያዩ ማኅበራዊ ማሻሻያዎችን አድርጓል።
በእነዚህ ለውጦች ምክንያትም ባለፉት አምስት ዓመታት በሠራተኛው ኃይል ውስጥ ያለው የሴቶች ተሳትፎ በእጥፍ ጨምሮ ወደ 33 በመቶ አድጓል። በባለፈው ዓመት የመጀመሪያው አጋማሽ ከወንዶች በበለጠ በርካታ ሴቶች ሠራተኛውን ኃይል ተቀላቅለዋል።
ሆኖም በአሜሪካ የተመሰረተው ብሩኪንግስ ተቋም ባለፈው ዓመት እንዳወጣው ጥናት ከሆነ አሁንም አብዛኞቹ በተለይ ደግሞ የሕዝብ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ያሉ የሥራ ቦታዎች በወንዶች የተያዙ ናቸው።
የስፔን የባቡር ድርጅት ያወጣው የሥራ ቅጥር በመንግሥት ሴክተር ውስጥ መስራት ከሚፈልጉ ሴቶች መካከል መቅጠር የሚችለው ጥቂቱን ብቻ ነው።
ምንም እንኳን ሳዑዲ አረቢያ ማኅበራዊ ማሻሻያዎችን ብታደርግም አሁንም ሴቶች ለማግባት፣ ከእስር ቤት ለመውጣት ወይም የጤና እንክብካቤ ለማግኘት የወንድ ጠባቂ ፈቃድ ያስፈልጋቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ሴቶች በጋብቻ፣ በቤተሰብ ጉዳይ፣ በፍቺ እና ከህጻናት ጋር በተያያዘ ለሚወሰን ውሳኔ አሁንም መገለል እንደሚደርስባቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።












