ከመድኃኒትና መድኃኒት ነክ ምርቶች የሚወጡ ተረፈ ምርቶች ለዓለም ጤና ስጋት ናቸው-ጥናት

የተበከለ ወንዝ

የፎቶው ባለመብት, Dr John Wilkinson

ከመድኃኒትና መድኃኒት ነክ ምርቶች የሚወጡ ተረፈ ምርቶች በዓለማችን የሚገኙ ወንዞችን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዱ እንደሆነና ከባቢ አየርንም ጭምር ስጋት ላይ እየጣሉ መሆናቸውን አንድ ጥናት ጠቆመ።

ፓራሴታሞል፣ ኒኮቲን፣ ካፌን፣ የሚጥል በሽታ እና የስኳር በሽታዎችን ለማከም ጥቅም ላይ የሚውሉ መድኃኒቶች ምርት ላይ ትኩረት አድርጎ የተሰራው ጥናት በመላው ዓለም አሳሳቢ ችግር ስለመኖሩ ጠቁሟል።

በምሳሌነትም በፓኪስታን፣ በኢትዮጵያ እና በቦሊቪያ የሚገኙ ወንዞች በከፍተኛ ሁኔታ መበከላቸው የተገጸ ሲሆን እንደ አይስላንድ፣ ኖርዌይ እና የአማዞን ደን ውስጥ የሚገኙ ወንዞች ደግሞ ከንጹሆቹ መካከል መሆናቸው ታውቋል።

የተለያዩ መድኃኒት አምራች ድርጅቶች የሚለቀቁ ንጥረ ነገሮች በወንዞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትሉ በሳይንስ ቢታወቅም እውነታው ግን ሌላ ነው። በርካቶች ስለጉዳቱ ምንም እውቀት የላቸውም።

ነገር ግን ከሁሉም በላይ ቀድሞ የሚመጣው በካይ ንጥረ ነገሮቹ በወንዞቹ ውስጥ የሚገኙ አሳዎች ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ነው።

ጥናቱ ከ1ሺህ በላይ በሚሆኑ ቦታዎች ላይ ተንቀሳቅሶ ከወንዞቹ ናሙናዎችን የወሰደ ሲሆን በዚህም ከ100 በላይ አገራት ተዳስሰዋል።

በአጠቃላይም 258 የሚሆኑት ወንዞች ከፍተኛ በሚባል ደረጃ የመድኃኒትና መድኃኒት ነክ ተረፈ ምርቶች ተገኝቶባቸዋል።

ይህም በውስጣቸው ለያዟቸው አሳ እንዲሁም ሌሎች እንስሳት ትልቅ ጠንቅ ነው።

"በዓለማችን እጅግ የተራቀቀ ቴክኖሎጂ ይጠቀማሉ የሚባሉት መድኃኒት አምራች ድርጅቶች እንኳን የሚጠቀሙት ማጣሪያ ሁሉንም ጎጂ ተረፈ ምርቶች የሚያጠፋ አይደለም። እነዚህ ተረፈ ምርቶች ደግሞ ተጣርተዋል ተብለው ነው ወደ ውሃ አካላት እንዲገቡ የሚደረገው" ይላሉ የጥናቱ ዋና አስተባባሪ ዶክተር ጆን ዊልኪንሰን።

የተበከለ ወንዝ

የፎቶው ባለመብት, Dr John Wilkinson

በሁሉም ወንዞች ውስጥ በሚባል ደረጃ በብዛት የሚገኙት ደግሞ ካርባማዜፒን የተባለው የሚጥል በሽታን ለማከም የሚውለው መድኃኒትና የስኳር በሽታን ለማከም ጥቅም ላይ የሚውለው ሜትፎርሚን የተባሉት መድኃኒቶች ተረፈ ምርቶች ናቸው።

እነዚህ ተረፈ ምርቶች ታዲያ ከወንዞች አልፈው ሰዎች በየዕለቱ ወደ ሰውነታቸው በሚያስገቧቸው እንደ ቡና እና ሲጋራ ምርቶች ውስጥ ጭምር እንደሚገኙ ጥናቱ ጠቁሟል።

አፍሪካ ውስጥ በሚገኙ ወንዞች ደግሞ በተለይ የወባ በሽታን ለማከም ጥቅም ላይ የሚውለው አርቲሚዚን የተሰኘው ንጥረ ነገር በበርካታ ወንዞች ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ተከማችቶ እንደሚገኝ ጥናቱ ያሳያል።

"እንደዚህ አይነት ነገሮች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመሩ እንጂ እየቀነሱ የሚሄዱ አይደሉም። ሰዎች ለሚያጋጥሟቸው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ችግሮች መድኃኒቶችን መጠቀም ይጨምራሉ እንጂ አያቆሙም" ይላሉ የጥናቱ አካል የሆኑት ዶክተር ቬሮኒካ ኤድመንድስ።

ጥናቱ እንደሚለው በወንዞች ውስጥ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች በብዛት የሚገኙ ከሆነ ወደፊት መድኃኒቶችን መቋቋም የሚችሉ ባክቴሪያዎች እንዲፈጠሩ በር እንዳይከፍት ተሰግቷል።

ይህ ደግሞ ከአካባቢያዊ ብክለት በተጨማሪ የመድኃኒቶችን ውጤታማነት በእጅጉ የሚቀንስ ነው።

በጣም ተበክለዋል የተባሉት ወንዞች በብዛት ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ በቂ ያልሆነ የማጣራት ሂደትና ቆሻሻዎችን ያለቅድመ ጥንቃቄ ወንዞች ውስጥ መጣል ነው።

ኬንያ ውስጥ የሚገኘው ናይሮቢ ወንዝ በዓለማችን በመድኃኒትና መድኃኒት ነክ ተረፈ ምርቶች በእጅጉ ከተበከሉ ወንዞች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።

ጥናቱ በመጨረሻም መንግሥታት መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ የመድኃኒት ምርት ቁጥጥር ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸውና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ተጠናከረው መቀጠል እንዳለባቸው ያሳስባል።