በእስር ላይ ያሉ የኦነግ አመራሮች በረሃብ አድማ ላይ መሆናቸው ተገለጸ

በእስር ላይ የሚገኙ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በረሃብ አድማ ላይ እንደሚገኙ ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።
በእስር ላይ የሚገኙ የኦነግ አመራሮችን ከሚወክሉት ጠበቆቻቸው መካከል አንዱ የሆኑት ቱሊ ባይሳ፤ የረሃብ አድማ ላይ የሚገኙት ሚካኤል ቦረን፣ ኬነሳ አያና፣ ዳዊት አብደታ፣ ለሚ ቤኛ፣ ገዳ ገቢሳ እና በቴ ኡርጌሳ የተባሉት የኦነግ አመራሮች መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እንደ ጠበቃው ከሆነ የተያዙበት ሁኔታ ሕጋዊ አይደለም በሚል ላለፉት አምስት ቀናት በረሃብ አድማ ላይ የቆዩት አመራሮቹ በአገር ሽማግሌዎች ተማጽኖ የረሃብ አድማቸውን ለማቆም ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ወደ ሆስፒታል ተወስደው አስፈላጊው የሕክምና መሳሪያ የለም ተብሎ ወደ እስር ቤት ከተመለሱ በኋላ በረሃብ አድማቸው መቀጠላቸውን አስረድተዋል።
"የረሃብ አድማውን ለማቆም ከአገር ሸማግሌዎች የቀረበላቸውን ተማጽኖ ተቀብለው ነበር። ነገር ግን ምግብ መውሰድ ከመጀመራቸው በፊት ወደ ሆስፒታል መወሰድ ነበረባቸው። ይሁን እንጂ በፌደራል ፖሊስ ሆስፒታል አስፈላጊ የሆነ የሕክምና መሳሪያ የለም በመባሉ ወደ ቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ እንዲመለሱ ተደርገዋል። አሁንም በረሃብ አድማ ላይ ናቸው" ብለዋል ጠበቃ ቱሊ ባይሳ።
የኦነግ አመራሮች በእስረኞች ላይ ያለውን አግባብ የሌለው አያያዝ በመቃወም የረሃብ አድማ እያደረጉ መሆኑን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በትናንትናው ዕለት ረቡዕ የካቲት 3፣ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
እስረኞቹ በአግባቡ እንደማይያዙና "እንግልትና ጥሰት ይፈጸምባቸዋል" ያለው መግለጫው ምግብ፣ ውሃና ሌሎች መሰረታዊ ሰብዓዊ አገልግሎቶችንም መነፈጋቸውንም አክሏል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች ምግብ በማቆማቸው "በጤንነትና አጠቃላይ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ደህንነት በየቀኑ እየተጎዱ ነው" ብሏል መግለጫው
ጠበቆችም ሆኑ የቤተሰብ አባላት እስረኞቹን ማግኘት ፈጽሞ አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው የሚናገሩት ጠበቃው የእስረኞቹን ሁኔታም ከደንበኞቻቸው ሳይሆን ታስረው ከሚለቀቁ ከሌሎች ሰዎች በተዘዋዋሪ የሚሰሙበት አጋጣሚዎች መኖራቸውን ይናገራሉ።
"እኛ (ጠበቆች) ከባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ እስካሁን አግኝተናቸው አናውቅም" በማለት ጠበቆች ከደንበኞቻቸው ጋር ከተገናኙ ወራቶች መቆጠራቸውን ያስረዳሉ።
ኦነግ በመግለጫውም የእስረኞቹ ቤተሰቦች እንዳይጠይቋቸው እንደሚከለከሉና አልፎ አልፎም ትንኮሳም እንደሚደርስባቸው በትናንትናው መግለጫ ሰፍሯል።
ጠበቃ ቱሊ እንደሚሉት ዐቃቤ ሕግ የኦነግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በሆኑት ሚካኤል ቦረን እና ኬነሳ አያና ላይ የማቀርበው ክስ የለኝም ብሎ መዝገባቸውን ከዘጋ አንድ ዓመት ቢያልፈውም አሁንም ሁለቱ ግለሰቦች በእስር ላይ እንደሚገኙ ያስረዳሉ።
ለሚ ቤኛ እና ዳዊት አብደታ የተባሉት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ደግሞ በፍርድ ቤት በነጻ የተሰናበቱ ናቸው ይላሉ ጠበቃው።
"ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ጠይቆ ኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ተከራክረን ነጻ የወጡ ሰዎች ናቸው። ፖሊስ ግን በሕገ-ወጥ መንገድ ይዟቸው ይገኛል" በማለት ቱሊ ያስረዳሉ።
እንደ ጠበቃው ከሆነ የኦነግ ቃል አቀባይ በሆኑት በቴ ኡርጌሳ እና የፓርቲው አመራር በሆኑት ገዳ ገቢሳ ደግሞ እስከነ ጭራሹ ክስ አልተመሰረተባቸወም፤ ሲከናወንባቸው የነበረው የወንጀል ምርመራ ተቋርጧል።
ኮሎኔል ገመቹ አያና እና የኦነግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አብዲ ረጋሳ ከትናንት በስቲያ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ፍርድ ቤቱ በነጻ ቢያሰናብታቸውም ዐቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ ግለሰቦቹ እንዳይለቀቁ አድርጎ አስቀምጧል ይላሉ።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ በትናንትናው መግለጫ ላይ" መንግሥት የኦነግ አመራሮችን በሕገ-ወጥ መንገድ በማሰር እና በእስር ቤቶች ውስጥ በማስቀመጥ እያሰቃየ ይገኛል" ብሏል።
ባለስልጣናቱ በኦነግ ለቀረበባቸው ክስ ምላሽ አልሰጡም።
መግለጫው አክሎም በእስር ላይ ያሉ አመራሮቹ በቡራዩ ፣ ሰበታ እና ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው እንደሚገኙ አመልክቷል።
"የተያዙበት ሁኔታ ከሞራልም ከሕግም ውጪ ነው"
ክስ ያልተመሰረተባቸውን፣ በፍርድ ቤት በነጻ የተሰናበቱና በሕግ መሠረት በእስር ላይ መቆየት የማይገባቸውን ከእስር ለማስፈታት "ሪፖርት ያላደረግንበት ቦታ የለም።" በማለት ጠበቃው ቱሊ ይናገራሉ።
"ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አሳውቀናል። አካልን ነጻ ማውጣት መዝገብ አስከፍተናል። . . . ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት አድርገናል" ይላሉ።
ቢቢሲ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን በተመለከተ ያነጋገረው አካል ስለመኖሩ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ጠበቃው ደንበኞቻቸው "የተያዙበት ሁኔታ ከሞራልም ከሕግም ውጪ ነው። . . . ከባድ ወንጀል ነው እየተፈጸመባቸው ያለው። ጉዳዩን ለቤተሰብም ማስረዳት በጣም አስቸጋሪ ሆኖብናል።" ይላሉ።
አብዛኞቹ የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ሁከትና ሽብርተኝነትን በማነሳሳት ተከሰው ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ ይገኛሉ።
አንዳንዶቹ እንዲፈቱ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም በእስር ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
መንግሥት በቅርቡ ለሚካሄደው አገራዊ ምክክር መንዱን ለማመቻቸት በሚል በእስር ላይ የነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ከእስር ፈትቷል።
ኦነግ ለአገራዊ ምክክሩ እንዳልተጠራ የገለጸ ሲሆን በዚህም ምክክር ለመሳተፍም አመራሮቹ እንዲፈቱ እየጠየቀ ነው።












