የኢራን ፖሊስ ፕራንክ ቪዲዮ ሰርተው ሶሻል ሚዲያ ላይ ያሰራጩ 17 ሰዎችን አሰረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢራን ፖሊስ በጎዳናዎች ላይ የተሰሩ ተከታታይ አስደንጋጭ የሐሰት ድርጊቶችን (ፕራንክ) የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን በኢንስታግራም ላይ ያሰራጩ 17 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አዋል።
የፕራንክ ቪዲዮዎቹን የሰሩት ግለሰቦች ግድያ የሚመስል አስደንጋጭ ድርጊት በመፈጸም እና የሰዎች ፊት ላይ ኬክ በመወርወር በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎችን ሲያስደነግጡ ታይተዋል።
ፖሊስ እነዚህ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የተከታዮቻቸውን ቁጥር ለማሳደግ ሲሉ በድርጊታቸው "ፍርሃትን ፈጥረዋል" ብሏል።
የኢራን ባለሥልጣናት በኢንተርኔት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርጉ ሲሆን፣ ፕራንክ አድራጊዎቹ የተያዙት ፖሊስ በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ሰፊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተከትሎ ነው።
በፖሊስ የተያዙት የኢንስታግራም ፕራንክ አድራጊዎች ድርጊቱ ሲፈጸም በስፍራው ለነበሩ ሰዎች እጅግ አስደንጋጭ ሐሰተኛ የግድያ ድርጊትና ኬክና አይስክሬምን የመሳሰሉ ነገሮችን በሰዎች ፊት ላይ በመወርወር ማስደንገጥና ማዋረድን ፈጽመዋል ተብሏል።
በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል አንዱ፤ የቀረጸውን ተንቀሳቃሽ ምስል ሶሻል ሚዲያ ላይ ከመጫኑ በፊት፤ ፕራንክ ከተደረገው ግለሰብ ፍቃድ መጠየቁን እና ለፈጠረው የስሜት መጎዳት 20 የአሜሪካ ዶላር ለመክፈል መስማማቱን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።
"ሰዎችን ማስደሰት እና የኢንስታግራም ተከታዮቼን ቁጥር መጨመር ብቻ ነው ፍላጎቴ" ሲልም ተናግሯል።
ሌላኛው በእስር ላይ የሚገኝ ፕራንክ አድራጊ ድርጊቱ ጥፋት መሆኑን በመረዳት መጸጸቱን ለኢራን መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል። "ፍቃድ ለመጠይቅ ጥያቄ ማቅረብ ነበረብኝ" ሲል ይቅርታ ጠይቋል።
ፖሊስ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከዚህ የተሻለ ማወቅ ነበረባቸው ይላል። "በቁጥጥር ሥር የዋሉት 17 ሰዎች በሙሉ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ትምህር መቅስማቸውን እና በታዋቂ ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ናቸው" ብሏል።
በቁጥጥር የዋሉት ግለሰቦች ላይ እስካሁን ክስ ስለመመስረቱ ግልጽ አይደለም።
ፖሊስ ፕራንክ አድራጊዎችን በቁጥጥር ሥራ ያዋለው ኢራን በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ከጀመረች በኋላ ነው።
ሐሙስ ዕለት ፖሊስ በቴህራን ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም "ውድመት እና አመጽን ያንጸባረቁ" ያላቸውን 94 ሰዎች ይዟል።
ከዚህ በተጨማሪም ፖሊስ "ትክክለኛ ያልሆኑ ባህሪያትን ያንጸባረቁ" ያላቸውን 16 ሰዎች በቁጥጥር ስር አውሎ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸውን መዘጋቱን አስታውቋል።












