በዩቲዩብ የሚቀርብ የባንክ ዘረፋ ፕራንክ ለመስራት የሞከሩት ወንድማማቾች ተፈረደባቸው

መንትዮቹ አሌክስና አላን ስቶክስ ስድስት ሚሊዮን የዩቲዩብ ተከታዮች አሏቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, መንትዮቹ አሌክስና አላን ስቶክስ ስድስት ሚሊዮን የዩቲዩብ ተከታዮች አሏቸው

ዩቲዩብ ላይ በርካታ ተከታይ ያላቸው ሁለት ወጣቶች ለተመልካቾች የሚያቀርቡትን ሐሰተኛ (ፕራንክ) የባንክ ዘረፋ ፈጽመው በታክሲ ለማምለጥ በሞክሩበት ትዕይንት ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኛ መሆናቸውን አመኑ።

ሁለቱ ወንድማማቾች አላን እና አሌክስ ስቶክስ በዩቲዩብ ቻናላቸው ላይ ስድስት ሚሊዮን ተከታዮች ያላቸው ሲሆን ለክስ የዳረጋቸውን ቀረጻ በሚያደርጉበት ጊዜ ነው አለመግባባት ተፈጥሮ የተያዙት።

ወንድማማቾቹ ሙሉ ፊታቸውን በጥቁር ጭምብል ሸፍነው የዘረፉትን ገንዘብ የያዙበት የሚመስል ቦርሳ ታቅፈው ለማምለጫ የሚሆን ታክሲ ቢጠሩም፤ ሁኔታውን የተመለከተውና ምን እየተካሄደ ያልተረዳው የታክሲ ሾፌር ወደ ፈለጉበት ቦታ ሊወስዳቸው አልፈቀደም።

ሁኔታውን የተመለከተ አንድ በአካባቢው የነበረ ግለሰብ ደግሞ ሁለቱ ወጣቶች የእውነት ባንክ ዘርፈው የታክሲውን ሾፈር በማስገደድ ሊያመልጡ የሚሞክሩ መስሎት ነበር።

ሁኔታው የእውነት የመሰላቸው ፖሊሶችም ከስፈራው ደርሰው ሽጉጥ በመደገን የታክሲውን አሽከርካሪ ከመኪናው እንዲወጣ በማዘዝ ክስተቱን ለመቆጣጠር ሞክሮ ነበር።

ሁለቱ ወንድማማቾች
የምስሉ መግለጫ, ሁለቱ ወንድማማቾች

ጉዳዩን የተመለከቱት በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ውስጥ የሚገኙት ዳኛ መንትዮቹ ወንድማማቾች ለፈጸሙት ድርጊት በገደብ የአንድ ዓመት የማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ ፈርደውባቸዋል።

ወጣቶቹ ከዓመት በፊት ተከታታይ የባንክ ዝርፊያ የሚመስሉ ፕራንኮችን የሰሩ ሲሆን ለዚህም ድርጊታቸው እስከ አምስት ዓመት ሊደርስ የሚችል እስራት ሊቀጡ ይችሉ ነበር።

"እንዲህ አይነቱ ድርጊት በቀላሉ ለሰዎች ሞት ወይም መጎዳት ምክንያት ሊሆን ይችል ነበር" ሲሉ ጉዳዩን የያዙት የአካባቢው ዐቃቤ ሕግ ቶድ ስፒትዘር ተናግረዋል።

እውነተኛ የባንክ ዘረፋ የበርካታ ሰዎችንና ፖሊሶችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ከባድ ወንጀል ነው ያሉት ዐቃቤ ሕጉ "እነዚህ ወጣቶች በዩቲዩብ ያላቸውን ተከታይ ለመጨመር ሲሉ የፈጸሙት ኃላፊነት የጎደለው የግዴለሽነት ድርጊት የታክሲ ሾፌሩንና የፖሊሶችን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው" ብለዋል።

ሐሰተኛ የዘረፋ "ፕራንክ ቪዲዮዎዎች" በዩቲዩብ ላይ በአንጻራዊነት የተለመዱ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ የውሸት የጦር መሳሪያዎችና የማምለጫ መኪኖች ጥቅም ላይ ይውላሉ።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ፖሊስ በሚደርስበት ጊዜ የሰውን ህይወት አደጋ ላይ የሚወድቅበት አጋጣሚ ይኖራል።

ባለፈው የካቲት ወር ቶሞቲ ዊልክስ የተባለ የ20 ዓመት ወጣት ሐሰተኛ የባንክ ዘረፋን በሚያሳይ የዩቲዩብ ቪዲዮ ቀረጻ ላይ እየተሳተፈ ሳለ በጥይት ተመትቶ ህይወቱ አልፏል።