ሴቶች በወንድ ሐኪሞች ቀዶ ሕክምና ሲደርግላቸው የመሞት ዕድላቸው ከፍ የሚለው ለምን ይሆን?

ሴት የቀዶ ሕክምና ሐኪም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሴቶች በወንድ ዶክተሮች የቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው የመሞት ዕድላቸው ከፍ ይላል በማለት አንድ ጥናት አመልክቷል። ለምን?

የቀዶ ሕክምና የሚያደርገውን ሐኪምዎ እርስዎ ላይ 'ኦፕሬሽን' ለማካሄድ ገዋን አጥልቆ ያስቡት እስቲ። በጭንቅላትዎ የሳሉት ሐኪም ሴት ወይስ ወንድ?

ሴት ከሆኑ የቀድ ጥገና ሐኪምዎ ሴት እንድትሆን ቢመኙ ይሻላል። ምክንያቱም በሕይወት የመቆየትዎ ዕድል የሰፋ ስለሆነ።

ይህን የምንልዎ ሴቶች በወንዶች ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው የመሞት ዕድላቸው 32 በመቶ ከፍ እንደሚል አንድ ጥናት ስለሚጠቁም ነው።

ነገር ግን ወንዶች የመሞት ዕድላቸው በሐኪሞቹ ፆታ ላይ ብዙም የተመሠረተ አይደለም።

ጥናቱ አክሎ ሴቶች በወንድ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ኦፕሬሽን ከተደረጉ ለሌላ ሕመም የመዳረጋቸው አሊያም በ30 ቀናት ውስጥ ተመልሰው ወደ ሆስፒታል የመምጣታቸው ዕድል የሰፋ ነው ይላል። እኮ ለምን?

'ጃማ ሰርጀሪ' በተሰኘው የሕክምና መፅሔት ላይ የወጣውን ጥናት የመሩት ዶክተር ክሪስቶፈር ዋሊስ ለዚህ ምክንያቱ ምን እንደሆ እርግጠኛ አይደሉም።

ለእነዚህ ጥያቄዎች እርግጥ የሆነ ምላሽ ባያገኙም ዶክተሩና አጋሮቻቸው ጥናታቸውን መቀጠላቸውን ዋሊስ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

እኛም የዚህን ጥያቄ ምላሽ ሐሰሳ ወደ ሴት የቀዶ ሕክምና አመራን። ለምን ይሆን ሴቶች በሴቶች እጅ ደኅንነታቸው የተጠበቀ የሆነው ብለንም ጠየቅን።

ስቃይን መረዳት

ጥናቱ በፈረንጆቹ ከ2007 እስከ 2017 ባለው ጊዜ በካናዳዋ ኦንታሪዮ ያሉ 1.3 ሚሊዮን ታካሚዎችን በመመርመር የተሠራ ነው።

በሐኪምና ታካሚ መካከል ስላለው የፆታ ልዩነትና የቀዶ ሕክምና ውጤት የተሠራ የመጀመሪያው ጥናት ነው ይላሉ አጥኚዎቹ።

አንድ በጥናቱ ላይ የተሳተፉ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ስቃይን የመረዳት ልዩነት አለ ይላሉ። ይህም ማለት ወንድ ሐኪሞች ሴቶች የሚሰማቸውን ስቃይ ላይረዱ ይችላሉ ማለት ነው።

ቦስተን የሚገኘው ተፍትስ የሕክምና ዩኒቨርሲቲ የሽንት ቦንቧ [ዩሮሎጂስት] ዶክተር የሆኑት ኦኒካ ዊሊያምስ በዚህ ይስማማሉ።

ዶክተር ኦኒካ ዊሊያምስ

የፎቶው ባለመብት, EMERSON HOSPITAL

የምስሉ መግለጫ, ዶክተር ኦኒካ ዊሊያምስ

"እኔ እንደሚመስለኝ ወንዶች የሴቶችን ቅሬታ ችላ ብለው ያልፋሉ። ሴቶች በጣም ጥንቅቅ ብለው ስለሚያስቡ ከቀዶ ሕክምና በኋላ ስለሚያቀርቡት ቅሬታ አትኩሮት የላቸውም። ቅሬታዎች በዋዛ ይታለፋሉ፤ ስቃያቸው ሰሚ ያጣል፤ የሕመማቸው መጠን ይረሳል" ይላሉ ዶክተሯ።

በኒው ዮርኩ ኖርዝዌል ኼልዝ ዩኒቨርሲቲ የደም ቧንቧ [ቫስኩላር] ቀዶ ሕክምና ሐኪም የሆኑት ዶክተር ጄኔፈር ስቫን ይህን ያስረግጣሉ።

ዶክተሯ እንደሚሉት ሴቶች የመሞት ዕድላቸው ከፍ የሚለው ወንድ ሐኪሞች የሴት ታካሚዎቻቸውን ስቃይ አሳንሰው ከማየታቸው የተነሳ ነው።

ለሐኪም ያለ አመለካከት

ዶክተር ናንሲ ባክስተር፤ በቶሮንቶ ቅዱስ ሚካኤል ኮሌጅ ሆስፒታል የኮሎሬክታል [የአንጀት ካንሰር] ቀዶ ሕክምና ባለሙያ ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት "ብዙ ሰዎች ሴቶች የሚሰማቸውን ስቃይ ከወንዶች ይልቅ የማጣጣል ልምድ አለባቸው።" ነገር ግን ሌሎችም ምክንያቶች ከግምት ውስጥ እንዲገቡ ያሳስባሉ።

"ታካሚ ስታይ እንደ ቀዶ ሕክምና ዶክተር ምንድነው ማድረግ ያለብሽ? ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍል ማንን ይዘሽ ነው የምትሄጅው? ወደ ኦፕሬሽን ክፍል የሚገቡት ሐኪሞች ፆታ ልዩነት ሊፈጥር ይችላል" ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

ዶክተር ናንሲ ባክስተር

የፎቶው ባለመብት, Unity Health Toronto

የምስሉ መግለጫ, ዶክተር ናንሲ ባክስተር

ዶክተሯ አንድ ጥናትን ዋቢ አድርገው እንደሚናገሩት ሴት የልብ ቀዶ ሕክምና ሐኪሞች ከወንድ ሐኪሞች በተሻለ ታካሚዎቻቸውን አድነዋል።

ቢሆንም ይላሉ ሐኪሟ፤ ለሴት እና ለወንድ ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ያለው አተያይም ከግምት ውስጥ መግባት አለበት።

"በቀዶ ሕክምና ክፍል ውስጥ ሴት ሐኪሞች መልካም ውጤት ካላመጡ ወቀሳ ይበዛባቸዋል። ለቀዶ ሕክምናዎች ላይመረጡም ይችላሉ። ይቅርታ የሚላቸው ሁላ ሊጠፋ ይችላል።"

"ነገር ግን ወንድ ሐኪሞች ባይሳካላቸው የሕክምና ውጤታቸው ከመጥፎ ዕድል ጋር ይያዛል" ይላሉ።

ተግባቦት

ሌላ እንደ ምክንያት ሊጠቀስ የሚገባው ጉዳይ ሴቶች ያላቸው "የላቀ ስሜታዊነት፣ ሐዘኔታ እና ከታካሚዎቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ነው" ይላሉ ዶክተር ኦኒካ።

የካንሳስ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ማዕከል የኦጥንት ቀዶ ሕክምና ሐኪም የሆኑት ዶክተር ኪም ቴምፕልተን ሴት ሐኪሞች ሴት ታካሚዎቻቸውን የሚያነጋግሩበት መንገድ ትልቅ ልዩነት ያመጣል ይላሉ።

ከዚህ በፊት የተሠሩ ጥናቶች እንሚጠቁሙት ታካሚዋ ሴት ሐኪሙ ደግሞ ወንድ ከሆነ በሐኪምና ታካሚ መካከል ያለው ግንኙነት ግልጽና የተሳለጠ ላይሆን ይችላል።

ይህ በታካሚና ሐኪም መካከል ያለው ግንኙነት የሐኪሙ ችግር ብቻ ላይሆን ይችላል።

ኦንታሪዮ የተሠራው ጥናት እንደሚያሳየው ሴት ታካሚዎች ከቀዶ ሕክምና በኋላ ስላሉባቸው ችግሮች ለወንድ ሐኪሞች ግልጥልጥ አድርገው ላይናገሩ ይችላሉ።

በዚህ የሚስማሙት ዶክተር ጄኔፈር "ሴት ታካሚዎች ወንድ ሐኪሞችን ስለማይደፍሯቸው ያለባቸውን ችግር በግልፅ ላይናገሩ ይችላሉ" ይላሉ።

ዶክተር ጄኔፈር

የፎቶው ባለመብት, Dr Jennifer Svahn

የምስሉ መግለጫ, ዶክተር ጄኔፈር

"የቀዶ ሕክምና ባለሙያ እመስላለሁ"

በርካታ ወንዶች ያሉበት የቀዶ ሕክምና ዘርፍ ፆታዊ መድልዎ እንዳለበት ሲነገር ቆይቷል፤ ዘርፉን ሴቶች እየተዉ የሚወጡትም ለዚያ ይሆናል።

በፈረንጆቹ 2015 ሴት የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ወደ ትዊተር አምባ አቅንተው #ILookLikeaSurgeon ["የቀዶ ሕክምና ባለሙያ እመስላለሁ"] የተሰኘ ዘመቻ ጀምረው ነበር።

ሴት የቀዶ ሕክምና ባሙያዎ ይህንን ዘመቻ የጀመሩት ብዙዉን ጊዜ ሰዎች "የቀዶ ሕክምና ባለሙያ አትመስይም" ስለሚሏቸው ይህንን አስተሳሰብ ለመቀየር በማለም ነው።

ዶክተር ኦኒካ "በርካታ ታካሚዎችና የሥራ አጋሮቼ ሳይቀሩ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ነች ብለው አይገምቱም" ይላሉ። "ብዙውን ጊዜ እኔ ረዳት እንደሆንኩ አሊያም ፀሐፊ፣ ዕድለኛ ከሆንኩ ደግሞ ነርስ አድርገው ነው የሚያስቡኝ።"

"አንዳንድ ጊዜ ራሴን ለታካሚዎች አስተዋውቄ፤ ስለሕመሙ አውርቼ፤ ከኦፕሬሽን በፊትና በኋላ ያለውን ሂደት አማክሬ ስጨርስ 'ማነው ኦፕሬሽን የሚያደርገኝ' የሚል ጥያቄ ይቀርብልኛል።"

ሐኪሞች በቀዶ ሕክምና ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፆታ አለመመጣጠን

ዶክተር ጀኔፈር ስቫን የሴት ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ቁጥር ማነስ ትልቁ ችግር እንደሆነ ያምናሉ።

"ሰዎች በሴት ሐኪሞች የመታከም ዕድላቸው ሴት ሐኪሞች ባለመኖራቸው ብቻ መጥበብ የለበትም" ይላሉ።

"ሴት ሐኪሞች ከወንዶች ይልቅ የተሻለ ቀዶ ሕክምና የሚያደርጉ ከሆነ - ምክንያቱ ምን ይሁን ምን - ሴቶች ይህን ዘርፍ ሊቀላቀሉ መንገዱም ሊቀልላቸው ይገባል" ባይ ናቸው።

ለምሳሌ ዩናይት ኪንግደም ውስጥ በርካታ ወንዶች ከሴቶች ይልቅ የቀዶ ሕክምናውን ዘርፍ መቀላቀልን ይመርጣሉ።

ይህንን ዘርፍ ተቀላቅለው በሥራው የሚቀጥሉ ደግሞ በርካታ ፆታዊ መድልዎ ይደርስባቸዋል። እንደ ዶክተር ኦኒካ ከሆነ ደግሞ ይህ ሁሌም የሚያጋጥማቸው ነገር ነው።

ይህንን ፈተና አልፎ በርካታ ሴቶች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ማድረግ ግን ለምርጫ ሊቀርብ አይገባም ባይ ናቸው።

ነገር ግን ለአሁኑ በርካታ ዶክተሮች እንደሚስማሙት "ሰዎች ስለቀዶ ሕክምና ባለሙያ ሲያስቡ ስለወንዶች ማሰባቸው መራሩ እውነታ ነው።"