ካሜሩን ወይስ ቡርኪና ፋሶ? ለዋሊያዎቹ አስጊ የሚሆነው ማነው?

የዋልያ ተጫዋች በሜዳ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለአንድ ዓመት የተራዘመው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እሑድ ጥር 01/2014 በካሜሩን ዋና ከተማ ያውንዴ ይጀምራል።

ኢትዮጵያ በምድብ 'ሀ' ከአዘጋጇ ካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶና ኬፕ ቬርድ ጋር ተደልድላለች። ካሜሩን በመጀመሪያው ጨዋታ ቡርኪና ፋሶን ስታስተናግድ፤ ዋሊያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን እሑድ ጥር 01 ምሽት 4 ሰዓት ከኬፕ ቬርድ ያደርጋሉ።

ሐሙስ ጥር አምስት ኢትዮጵያ ሁለተኛ ጨዋታዋን ከአዘጋጇ ካሜሩን ጋር ስታደርግ በዚያኑ ቀን ኬፕ ቬርዴ ቡርኪና ፋሶን ትገጥማለች።

በሦስተኛውና በመጨረሻው የምድቡ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡርኪና ፋሶን ስትፋለም ካሜሩን ደግሞ ከኬፕ ቬርዴ ትገጥማለች።

የውድድሩ አዘጋጅ ካሜሩን በአፍሪካ ዋንጫ በመሳተፍ ከምድቡ ሃገራት የሚያክላት የለም።

ቡርኪና ፋሶ ለ12ኛ ጊዜ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በአንድ ዝቅ ብላ ለ11ኛ ጊዜ ትሳተፋለች። ለውድድሩ እንግዳ ያልሆነችው ኬፕ ቨርዴ የዘንድሮ ተሳትፎዋ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

ከኢትዮጵያ በቀር ሁሉም የምድቡ ሃገራት በአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾቻቸውን ይዘው ነው ወደ ካሜሩን ያቀኑት።

ነገር ግን ከሽመልስ በቀለና ሙጂብ ቃሲም በቀር ሁሉንም ተጫዋቾቿን ከሃገር ውስጥ ክለቦች የመረጠችው ኢትዮጵያ የውድድሩ ክስተት ልትሆን እንደምትችል ብዙዎች ይገምታሉ።

ኢትዮጵያ (ካሌብ ሞገስ፣ ከቢቢሲ አማርኛ እንደጻፈው)

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ የደረሰችው ከዘጠኝ ዓመታት ቆይታ በኋላ ነው።

በ1962 (እአአ) የአህጉሪቱን ትልቁን ዋንጫ ያነሱት ዋሊያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፉ ይህኛው ለ11ኛ ጊዜ ነው።

በዓለም እግር ኳስ 137ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በአሠልጣኝ ውበቱ አባተና በአምበሉ ጌታነህ ከበደ እየተመራች ወደ ያውንዴ አቅንታለች።

ይህ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለአሠልጣኝ ውበቱ አባቱና ለቡድኑ አባላት ከአፍሪካ ዋንጫ መሥራቾች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ያላትን ተሰጥዖ የሚያሳዩበት መድረክ እንደሚሆን ይገመታል።

ውበቱ ለዓይን ገዥ የሆነውን ኳስ እግር ላይ ሳይቆዩ እየተቀባበሉ መጫወትን የሚመርጥ አሠልጣኝ ነው።

የመሃል ሜዳው ሞተር ሽመልስ በቀለና አጥቂው ጌታነህ ከበደ ከወጣቱ የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ አቡበከር ናስር ጋር በመጣመር ለተቀናቃኞቻቸው አደጋ ሊሆኑ ይችላሉ።

ውበቱ በሚመርጠው የ4-3-3 አሠላለፍ ማለትም 4 የኋላ ደጀን ሦስት አማካዮችና ሦስት አጥቂዎች ተመርቶ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይገመታል።

ብሔራዊ ቡድኗን በውበቱ አባተ እያጠናከረች ያለችው ኢትዮጵያ ወደ ዙር 16 መሻገር እንደ ትልቅ ውጤት ቢታይ የሚገርም አይሆንም።

አዘጋጇ ካሜሩንና ቡርኪና ፋሶ ለኢትዮጵያ ፈታኝ ሊሆን የሚችሉ ቡድኖች እንደሚሆን ይገመታል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አውሮፓ የሚጫወቱ ተጫዋቾቿን ይዛ በእግር ኳስ የተሻለ ውጤት እያመጣች ያለችው ኬፕ ቨርድም ቀላል ግምት የሚሰጣት አይደለችም።

ከሁሉም ብሔራዊ ቡድኖች ቀድመው ወደ ካሜሩን ያቀኑት ዋሊያዎቹ በተሻለ የመንፈስ ጥንካሬ ላይ እንደሚገኙ እየተነገረ ነው።

አልፎም ብሔራዊ ቡድናቸው በአፍሪካ ትልቁ ውድድር ሲሳተፍ ማየት ለጓጉ ኢትዮጵያዊያን ይህ ትልቅ ዕድል ነው።

ካሜሩን (የካሜሩን ራድዮ ቴሌቪዥን የስፖርት ክፍል ኃላፊ ኒጂዬ ኢናው እንደፃፈው)

በፈረንጆቹ 2017 ካሜሩን ግብፅን በመርታት የአፍሪካ ዋንጫን ስታነሳ የማሸነፊያዋን ግብ ያስቆጠረው ቪንሴንት አቡበከር ነበር።

የአፍሪካ ዋንጫን አምስት ጊዜ ያነሳችው ካሜሩን በውድድሩ የምትሳተፈው ለ20ኛ ጊዜ ነው። በአሠልጣኝ አንቶኒዮ ኮንሴያኮና በአምበሉ ቪንሲኔት አቡበከር ትመራለች።

በዓለም የብሔራዊ ቡድኖች ደረጃ 50ኛ ላይ የተቀመጠችው ካሜሩን የምትዘጋጀውን ዋንጫ በማንሳት የአፍሪካ ዋንጫ ቁጥሯን ወደ ስድስት ለማሳደግ ነው።

ኳስን ይዞ በመጫወት የሚታወቁት ፖርቱጋላዊው አሠልጣኝ አንቶኒዮ ኮንሴያኮና ቡድኑን የተረከቡት መስከረም 2019 ነበር።

አንቶኒዮ ቡድኑን ከተረከቡት በኋላ ካሜሩን ጫና በማሳደር የምትጫወት ሲሆን በግራና በቀኝ ክንፍ የሚሰለፉ ተጫዋቾች በማጥቃትና በመከላከል የጎላ ሚና እንዲኖራቸው ይጠበቃል።

የማይበገሩት አናብስት መሃል ላይ የናፖሊውን አንድሬ-ፍራንክ ዛምቦ አንጊሳን አሰልፈው ኳስ ይዘው እንደሚጫወቱ ይጠበቃል።

የባየር ሙኒኩን ኤሪክ ቹፖ-ሞቲንግ እንዲሁም የሊዮኑ ካርል ቶኮ ኢካምቢ የማጥቃት ኃላፊነቱን ይወስዳሉ።

ለአንድ ዓመት ያክል በቅጣት ምክንያት ከእግር ኳስ ርቆ የነበረው የአያክስ አምስተርዳሙ ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና የአንቶኒዮ ምርጫ እንደሚሆን እሙን ነው።

ቡርኪና ፋሶ (የስፖርት ጋዜጠኛው ማሳቫዎ ቢላ እንደፃፈው)

የቡርኪና ፋሶው አጥቂ በርትራንድ ትራኦሬ ለሁለት ወራት ያክል በጉዳት ከሜዳ ርቆ ባለፈው ሳምንት ነበር ለአስተን ቪላ የተሰለፈው።

በአሠልጣኝ ካሙ ማሎና በአምበሉ ኢሶፉ ዳዮ የምትመራው ቡርኪና ፋሶ ለ12ኛ ጊዜ ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ የምትሳተፈው በ2013 (እአአ) ለዋንጫ ደርሳ መረታቷ አይዘነጋም።

ልክ እንደተቀሩት የምድቡ ቡድኖች ቡርኪና ፋሶ ወደ ቀጣዩ ዙር ልታልፍ ትችላለች የሚል ግምት ተሰጥቷታል።

በወጣት ተጫዋቾች የተሞላው የካሞ ቡድን እነ ሀርቬ ኮፊ፣ ኤድሞንድ ታፕሶባ፣ ኢሳ ካቦሬ እንዲሁም በርትራንድ ትራኦሬና ጉስታቮ ሳንጋሬ ጎልተው የሚወጡት ውድድር ሊሆን ይችላል።

ከዚህም በተጨማሪ ቡርኪና ፋሶ ለብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የመንፈስ ጥንካሬ በማለት የሥነ-ልቡና አማካሪ ይዘው ነው ወደ ካሜሩን የሚያቀኑት።

ኬፕ ቬርድ

(የቀድሞው የኬፕ ቬርድ አሠልጣኝ ሉሲዮ አንቱኔዝ እንደፃፉት)

ኬፕ ቨርድ ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈችው በፈረንጆቹ 2015 ነበር።

ለሦስተኛ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የምትሳተፈው ኬፕ ቬርድ በአሠልጣኝ ቡቢስታና በአምበሉ ሪያን ሜንዴዝ ትመራለች።

ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፉ በአፍሪካ እንዲሁም በአውሮፓ መነጋገሪያ የነበሩት ሰማያዊ ሻርኮቹ፣ በዓለም የብሔራዊ ቡድኖች ደረጃ 73ኛ ላይ ተቀምጠዋል።

ካቦ ቬርድን በእግር ኳስ ትልቅ ደረጃ ለማድረስ ቆርጦ የተነሳው የአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህ ተሳክቶለት በፊፋ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ከነበረበት 126ኛ ደረጃ ወደ 73ኛ ማሳደግ ችሏል።

ምንም እንኳ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ለአፍሪካ ዋንጫ አዲስ ቢሆኑም የውድድሩ ክስተት ሊሆን እንደሚችሉ እገምታለሁ።

ኬፕ ቨርድ ያለችበት ምድብ ጠንካራ ቢሆንም በአሠልጣኙ ልምድ በመታገዝ ጥሩ ውጤት ሊያስመዘግቡ እንሚችሉ ይገመታል።

ለካሜሩን ቡድን ከፍያለ ግምት ያላቸው ሲሆን፣ ከቡርኪና ፋሶ ጋር በመፎካከር ከምድቡ የሁለተኛ ደረጃን የማግኘት ፍላጎት አላቸው። ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ ቡድንን የሚንቁት አይደለም።

በዚህም ከምድብ ውድድር ባሻገር ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋን የያዙት ኬፕ ቬርዶች ከዚያም ያለፈ ውጤት ለማስመዝገብ የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል።