"ድንገት አመሻሹ ላይ ነው ዕቃችሁን ይዛችሁ ውጡ የተባልነው" የባልደራስ አመራር

አቶ እስክንድር ነጋና አቶ ስንታየሁ ቸኮል

የፎቶው ባለመብት, Social Media

የምስሉ መግለጫ, አቶ እስክንድር ነጋና አቶ ስንታየሁ ቸኮል ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ

በዛሬው ዕለት ከእስር የተፈቱት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስለመፈታታቸው ቀደም ሲል ምንም አይነት መረጃ እንዳልነበራቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።

የባልደራስ ከፍተኛ አመራር የሆኑትና በቂሊንጦ ከአቶ እስክንድር ነጋ ጋር ታስረው የነበሩት የፓርቲው የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል በዛሬው ዕለት ከምሽቱ 12፡30 አካባቢ የማረሚያ ቤቱ ሠራተኞች ድንገት መጥተው ከማረሚያ ቤቱ እንዲወጡ እንደነገሯቸው አስስረድተዋል።

"ድንገት አመሻሽ ላይ መጥተው ዕቃችሁን ይዛችሁ ውጡ አሉን፤ ያው እቃችንን ይዘን ወጣን። ምንም የምናውቀው ነገር የለም" በማለት አቶ ስንታየሁ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንደወጡ በስልክ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ አቶ ስንታየሁን በስልክ ባገኘበት ወቅት ከቂሊንጦ ማረሚያ ወጥተው ከአቶ እስክንድር ጋር ከማረሚያ ቤቱ አቅራቢያ ወደሚገኝ ቤተ ክርስቲያን እያመሩ እንደሆነም ገልጸዋል።

"በዋናነት የተፈታነው በአምላክ ኃይል ነው፤ እውነት ነው ያሸነፈው፤ የሕዝብ ትግል፣ የሕዝብ እንባ ነው ያሸነፈው" ብለዋል።

የታዋቂው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከተነሳው ሁከት ጋር ተያይዞ ለእስር ተዳርገው የነበሩት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የተፈቱት በአሁኑ ወቅት ክሳቸው ተቋርጦ ወይስ በምን ሁኔታ እንደሆነ ቢቢሲ አቶ ስንታየሁን ጠይቋቸው ነበር።

"እኛ የምናውቀው ነገር የለም፤ ነገር ግን ክሱን አቋርጠውት ሊሆን እንደሚችል ግምት መውሰድ ይቻላል። የወጣነው ደብዳቤ መጥቶ ነው የተባለው። ስንታሰርም በትዕዛዝ ነው የታሰርነው፣ ስንወጣም በትዕዛዝ ነው። ይሄ ማሳያ ነው። ስለዚህ ውጡ ነው የተባልነው ወጣን" በማለት መልሰዋል።

"በሐሰት ተከሰን ነው የመጣነው የግፍ እስረኞች ነን" ያሉት አቶ ስንታየሁ "ሕዝቡ ይህንን በሚገባ ያውቃል የእኛን ጥያቄ ሕዝቡ ስለሚረዳው የሕዝቡ ፀሎት ነው አሸንፎ ዛሬ የወጣነው እስከ ህይወታችን ምዕራፍ ድረስ የሕዝቡን ጥያቄ ይዘን እንታገላለን" በማለት መልሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ምን አይነት ስሜት እየተሰማቸው እንደሆነ ቢቢሲ አቶ ስንታየሁን ጠይቋቸዋል "በዚህ አንድም ስብራት የለብንም የበለጠ ተጠናክረን ነው ወደ ትግሉ የምንገባው፤ የበለጠ ከነማን ጋር ተሰባስበን ልንታገል እንደምንችል የፈተሽንበት እንዲሁም ያየንበት ነው። የበለጠ ትግሉን እንደሚያጠናክረው ነው" ብለዋል።

አቶ እስክንድር ነጋና ሌሎች የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በታዋቂው ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ ከተቀሰቀሰው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየታየ ነበር።

ከእነ አቶ እስክንድር በተጨማሪ ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራር የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ከ20 በላይ ተከሳሾችም የሐጫሉን ግድያ ተከትሎ ከተከሰተው ሁከት ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የነበሩ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ከእስር እንዲፈቱ ውሳኔ ተላልፏል።

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ከአንድ ዓመት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ መኪናው ውስጥ ሳለ በጥይት ተመትቶ መገደሉን ተከትሎ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል የበርካታ ሰዎች ህይወት ያለፈበትና ከፍተኛ ንብረት የወደመበት ሁከት መከሰቱ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ ካለመረጋጋቱ ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ጨምሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቷል።

የፍትህ ሚኒስቴር ከአመሻሹ ባወጣው መግለጫ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሕገ-መንግስት እና የሽብር ችሎት እየታየ ከነበሩት ተከሳሾች መካከል በነጃዋር ሲራጅ መሃመድ እና በእነ እስክንድር ነጋ ፈንታ መዝገብ ያሉ ተከሳሾች ክሳቸው በአዋጅ ቁጥር 943/2008 መሰረት እንዲነሳ ተደርጓል ብሏል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ባሰፈረው መሰረት ክሱ እንዲነሳ የተደረገው" በቀጣይ የሚደረገውን ሃገራዊ የምክክር መድረክ ሂደት ውጤታማነት እና አካታችነት ከፍ ለማድረግ በማሰብ ነው።" ብሏል።