አቶ አስክንድር በእስር ቤት በተፈጸመባቸው ድብደባ ምክንያት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀሩ

ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት አቶ እስክንድር ነጋ በማረሚያ ቤት ውስጥ ደረሰባቸው በተባለ ድብደባ ምክንያት ዛሬ በነበራቸው የችሎት ቀጠሮ ላይ ሳይገኙ መቅረታቸው ተገለጸ።
ከአንድ ዓመት በላይ በአስር ቤት የቆዩት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አስክንድር ነጋ፣ ከሌሎች ሦስት የፓርቲያቸው አባላት ጋር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸውን እየተከታተከሉ መሆኑ ይታወቃል።
ከረዥም የፍርድ ቤት ሂደት በኋላ በአቶ አስክንድር እና በሌሎች ተከሳሾች ላይ የቀረቡ ምስክሮች መሰማት የጀመሩት ረቡዕ ጥቅምት 10/2014 ዓ.ም የነበረ ቢሆንም፣ ባጋጠማቸው ችግር ምክንያት ችሎቱ አለመቀጠሉን ጠበቃዎቻቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከአቶ አስክንድር ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ በዛሬው ችሎት እንዳልቀረቡ ገልጸው ለዚህም ምክንያቱ በአንድ ታራሚ በተፈጸመባቸው ድብደባ ሳቢያ መሆኑን አመልክተዋል።
ጠበቃው ጨምረውም በአቶ እስክንድር ላይ ድብደባው የተፈጸመው "ከዚህ ቀደም ይዝትባቸው ነበር" ባሉት ታራሚ አማካኝነት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
በዛሬው ችሎት ከአቶ አስክንድር ጋር የተከሰሱት የፓርቲው አባላት ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ የቀረቡ ሲሆን አቶ አስክንድር ያልተገኙበትን ምክንያትን አቶ ስንታየሁ አስረድተዋል።
በዚህም አቶ አስክንድር ላይ በአንድ ታራሚ ድብደባ እንደተፈጸመባቸውና በዚህም ምክንያት ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የማረሚያ ቤቱ ተወካይ ረቡዕ አመሻሽ ላይ ከአንድ አስረኛ ጋር በተፈጠረ ፀብ ምክንያት፣ ሐሙስ ጠዋት ወደ ፍርድ ቤት በቀጠሯቸው መሰረት እንዲሄዱ ቢጠየቁም አቶ አስክንድር መሄድ እንደማይፈልጉ መግለጻቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
የማረሚያ ቤቱ ተወካይ እንዳሉት አቶ እስክንድር በተፈጸመባቸው ድብደባ ጉልበታቸው ላይ መቁሰላቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን ይህ ፍርድ ቤት ለመቅረብ የሚከለክላቸው አለመሆኑንና ለመቅረብ ባለመፈለጋቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
በአቶ እስክንድር ነጋ ላይ ደረሰባቸው ስለተባለው ድብደባ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች በኩል ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ቢቢሲ ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ስልክ ባለመነሳቱ ምክንያት አልተሳካም።
ጠበቃ ሰለሞን እንዳሉት ረቡዕ የተጀመረው ችሎት፣ ሐሙስም እንዲቀጥል በተያዘው ቀጠሮ መሠረት ቢሆንም አንደኛ ተከሳሽ አቶ እስክንድር ነጋ ሳይቀርቡ በመቅረታቸው ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ እና የተከሳሽ ጠበቆችም በጉዳዩ ላይ አስተያየት አንዲሰጡ ካደረገ በኋላ የምስክር መሰማቱ ሂደት ለመቀጠል ለመጪው ሰኞ ጥቅምት 15/2014 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።
በእነ አቶ እስክንድር ነጋ መዝገብ፤ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ይቅረቡ ወይስ በግልጽ ችሎት ይቅረቡ የሚለው ክርክር በሰበር ሰሚ ችሎት የታየ ሲሆን ምስክሮች በግልጽ ችሎት ይቅረቡ በሚል ውሳኔ መቋጨቱ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የፀረ ሽብርና ሕገመንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አመራሮች መዝገብ ዐቃቤ ሕግ የምስክሮችን ስምና አድራሻ በመገናኛ ብዙኃን እንዳይቀርቡ ሲል ያቀረበውን አቤቱታ ውድቅ ማደረጉ ይታወቃል።
ዐቃቤ ሕግ በታዘዘው መሰረት ከዘጠኝ ምስክሮች ዝርዝር በተጨማሪ አሉኝ የሚላቸውን 21 ምስክሮች ዝርዝር ለጥቅምት 10 ቀን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቶት ምስክሮችን የመስማት ሂደት ተጀምሮ ነበር።
አቶ እስክንድር ነጋና ሌሎች የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት በ2012 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ በታዋቂው ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ ከተቀሰቀሰው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ ይገኛሉ።












