የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ያለሙት የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች

የፎቶው ባለመብት, Addis Ababa Press Secretary/FB
በተለያዩ ምክንያቶች በኢትዮጵያ በሚገኙ ከተሞች የመሠረታዊ ምርቶች ዋጋ ያለማቋረጥ እያሻቀበ ዜጎች ላይ ጫና እየፈጠረ ነው።
ለዋጋ ግሽበቱ ምክንያት በመሆን ከሚጠቀሱት መካከል በአገሪቱ ያለው ጦርነት እና ያስከተላቸው ጊዜያዊ ችግሮች እንዲሁም በወጪ ንግድ ያለው መዛነፍ ይጠቀሳሉ።
በሌላ በኩል በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ እና በሌሎች ዓለም አቀፋዊ የምጣኔ ሀብት ምክንያቶች በኢትዮጵያ ኑሮ 'የማይቀመሰ' ሆኗል የሚለውን ብዙዎች የሚጋሩት ነው።
ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው የኅዳር ወር 2014 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ33 በመቶ ጭማሪ አለው።
ከዚህ ውስጥ የምግብ ነክ ምርቶች የኅዳር ወር በ38.9 በመቶ የጨመረ ሲሆን አምና በተመሳሳይ ወቅት ተንከባላይ የምግብ ነክ ዋጋ ግሽበት 23.2 ሆኖ ተመዝግቦ ነበር። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተብ ክፍሎች ደግሞ በዋጋ ግሽበቱ በቀዳሚነት ተጎጂ ሆነዋል።
እነዚህን የኅብረተብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ የቅዳሜ እሁድ ገበያዎች ከሳምንታት በፊት ሥራ ጀምረዋል።
ገበያዎቹ ለምን ተቋቋሙ?
ገበያዎቹ በአንድ በኩል ለሸማቾች ምክንያታዊ በሆነ ዋጋ ምርት የማቅረብ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለአምራቾች ገበያ የመፍጠር ዓላማ ያላቸው ናቸው።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ ላለፉት ዘጠኝ ሳምንታት በአዲስ አበባ የተለያዩ አከባቢዎች የተከናወኑት የእሁድ ገበያዎች ቀዳሚ ዓላማ በከተማው የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት "ለመከላከል እና ለመቆጣጠር" እንዲሁም ሸማቾችን እና አምራቾችን በቀጥታ ለማገናኘት ያለመ እንደሆነ ይናገራሉ።
"በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን ማግኘት እንዲችሉ እና ከዚያ ጎን ለጎን ደግሞ ለአምራች፣ አርሶ አደሮችም፣ ፋብሪካዎችም የገበያ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ያለመ ነው።...ከተማችን ላይ ያለውን የምርት አቅርቦት መጠን ማሳደግም" ዓላማው ነው ሲሉ ለቢቢሲ አብራርተዋል።
በአዲስ አበባ ይህ ገበያ በየሳምንቱ እሁድ የሚደረግ ሲሆን በድሬዳዋ ደግሞ ቅዳሜንም ያካትታል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የድሬዳዋ ከተማ የንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሚኑ ጠሃ፣ የገበያዎቹ "ዋና ዓላማ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ነው። በተለይ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ዋጋ ሳይጨመርበት የግብር ምርቶችን እና የፋብሪካ ምርቶችን በቀላሉ በተመጣጣኝ ዋጋ አግኝቶ ከኑሮ ጫናው እንዲላቀቅ የተጀመረ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
ገበያዎቹ ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባሉ የሚሉት አቶ አሚኑ፣ የሽንኩርትን ገበያ ለአብነት በማንሳት "በመደበኛው ገበያ እስከ አርባ ብር የሚሸጠው ሽንኩርት እኛ ባዘጋጀነው የቅዳሜ እና የእሁድ ገበያ እስከ 28 ብር የሚሽጥ ነው" ብለዋል።
በገበያዎቹ ምን እና ማን ያቀርባል?
በአዲስ አበባ በአስራ አንድ፣ በድሬዳዋ ደግሞ በአራት ቦታዎች የተዘረጉት እነዚህ የእረፍት ቀናት ገበያዎች የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶች የሚቀርቡበት ነው።
በሁለቱም ከተሞች ያሉ የከተማ ግብርና ውጤቶች እንዲሁም በከተሞቹ ዙሪያ ያሉ አርሶ አድሮች የሚያመርቷቸው የእህል ምርቶች በገበያዎቹ አማካኝነት ለነዋሪዎች ይቀርባል።
በድሬዳዋ ከተማ እነዚህ ገበያዎች በአብዛኛው ጤፍን ጨምሮ አትክልት እና ፍራፍሬ፤ ከቃሪያ እስከ ሽንኩርት ያሉ የጓሮ አትክልቶችን እንዲሁም በከተማ ውስጥ ያሉ ፋብሪካዎች የሚያመርቷቸው ዘይት፣ ዱቄት፣ መኮሮኒ፣ ፓስታ፣ ብስኩትን እና ሳሙናን የመሰሉ ምርቶች ይቀርቡበታል።

የፎቶው ባለመብት, Addis Ababa Press Secretary/FB
የፋብሪካ ምርቶቹ "በተመጣጣኝ ዋጋ ኅብረተሰቡ ማግኘት እንዲችል ነው፤ አከፋፋይ እና ቸርቻሪ እጅ ሳይገባ ማለት ነው። በፋብሪካ ዋጋ ኅብረተሰብ እንዲያገኝ የተደረገ ነው" ሲሉ አቶ አሚኑ ተናግረዋል።
እንደ ድሬዳዋ ሁሉ በአዲስ አበባም በገበያዎቹ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ይቀርቡበታል። ገበያዎቹ እንደ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ጎመን ያሉ አትክልቶች፤ ሙዝ እና ብርቱካንን የመሳሰሉ ፍራፍሬዎች፤ ጤፍ እና ስንዴን ጨምሮ የሰብል ምርቶች፤ ዘይት፣ ፓስታ፣ የዳቦ ዱቄት አይነት የኢንዱስትሪ ውጤቶችንም የሚያካትት ነው።
"በዋናነት ምርቶቹ ትኩረት ያደረጉት ኅብረተሰቡ በየዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ለምግብነት የሚያውላቸው እና የሚጠቀምባቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በአቅራቢያው እንዲያገኝ ያለመ" እንደሆነ አቶ መስፍን ጠቅሰዋል።
ለገበያዎቹ ምርት የሚያቀርቡት በከተማ ግብርና የተሰማሩ በግልም ይሁን ተደራጅተው የሚሰሩ አምራቾች ናቸው። በተጨማሪም በከተሞቹ ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮች እና ፋብሪካዎች ናቸው።
ከተሞቹ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከደቡብ ክልል የሚገኙ ምርቶችን በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች አማካኝነት ያቀርባሉ።
ገበያዎቹ እስከመቼ ይቀጥላሉ?
በድሬዳዋ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ በተጀመረ በአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ውስጥ ወይም እስከ 6ኛው ሳምንት አርባ ሚሊዮን ብር የሚያህል ግብይት መፈጸሙን አቶ አሚኑ ተናግረዋል።
"በዚህ ስድስት ሳምንት ውስጥ አርባ ሚሊዮን ግብይት ቢካሄድም ግን በመደበኛ የገበያ ዋጋ ሊያወጣ ይችል የነበረው ከአስር ሚሊዮን ብር በላይ ኅብረተሰቡን አድነነዋል" ብለዋል ኃላፊው።
የገበያ ልውውጡን ትክክለኛው አሀዝ መረጃ ለጊዜው የለኝም ያሉት አቶ መስፍን ደግሞ ልውውጡ "ሰፊ ቁጥር ያለው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ" መምጣቱን ጠቅሰው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
"ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት እየገነባን እስክንሄድ፣ የቁጥጥር ሥርዓታችን ውጤታማ እየሆነ ሲሄድ፣ ምርታማነታችንን በምንፈልገው ደረጃ እስኪደርስ ... ገበያዎቹ ተጠናክረው ይቀጥላሉ" የሚሉት አቶ መስፍን እነዚህ የመገበያያ አማራጮች የሚይዟቸው ምርቶች እያደጉ ቦታዎቹም እየጨመሩ እንደሚሄዱም አመላክተዋል።
በድሬዳዋ ደግሞ በስሩ ያሉ ሁሉም ቀበሌዎች ለእነዚህ የገበያ አማራጮች ስፍራዎችን እንዲያዘጋጁ እየተደረገ መሆኑን አቶ አሚኑ ተናግረዋል። ገበያዎቹ አሁን በያዙት ቅርጽ ወይም ተጨማሪ አማራጮችን በማካተት በዘላቂነት እንሚቀጥሉም አንስተዋል።
ኃላፊዎቹ እነዚህ ገበያዎች የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የቀረቡ አማራጮች መሆኑን ጠቅሰው፣ ሰፊው ገበያ ላይ የሚስተዋሉ እና ዜጎች ላይ ጫና እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ የንግድ ሥርዓቱ ችግሮችን ለመቅረፍ የተጀመሩ ቁጥጥሮች እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።















