የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ከፍተኛ መጠን ያለው የስንዴና ዘይት ግዢ መፈጸሙ ተገለጸ

የእህል ገበያ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

በኢትዮጵያ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት 4 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴና 12.5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ግዢ መፈጸሙን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ግዢው የተፈጸመው በጥቅምትና ኅዳር ወራት ሲሆን ከተገዛው 4 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኩንታል ስንዴ ወደ አገር ውስጥ መግባቱም ተገልጿል።

የተቀረውም ስንዴ በተቻለ ፍጥነት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በሂደት ላይ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ የስንዴ ዋጋንም ከፍ እንዳይል የራሱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብሏል ገንዘብ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ዛሬ ታኅሣሥ 26/2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ።

ግዢ የተፈጸመበት 12.5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።

ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴና ዘይት ግዢ መፈጸሙ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠርና የገበያ ዋጋን በማረጋጋት ረገድ ፋይዳ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን የተረጋጋ ማክሮ ምጣኔ ሀብት ከማስፈን አንፃርም ሚና ይጫወታል ተብሏል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና የተጠሪ ተቋማት የመቶ ቀን እቅድ አፈጻጸም ግምገማ በተካሄደበት ወቅት ነውም ይህንን የገለጸው።

በተጨማሪም ዘይትና ዱቄት አስመጪዎች በራሳቸው የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገቡ በመደረጉ የሸቀጦች ዋጋ ባለበት እንዲቀጥል አስችሏልም ተብሏል።

በሰሜኑ ጦርነትና በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት የዋጋ ግሽበት አስከትሎባታል በተባለችው ኢትዮጵያ በተወሰነ መልኩ መቀነስም አሳይቷል ተብሏል።

በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር 34.2 በመቶ የነበረው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በኅዳር ወር ወደ 33.0 በመቶ ዝቅ ብሏል።

በተጨማሪም በ2014 በኅዳር ወር የምግብ ዋጋ ግሽበት ከጥቅምት ወር ጋር ሲነጻጸር በ1.8 በመቶ የቀነሰ ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት 1.0 ከመቶ የጨመረ መሆኑን መረጃው ጠቁሟል።