ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳር እና ሩዝ ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆኑ ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
የተወሰኑ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላልተወሰነ ጊዜ ከቀረጥና ታክስ ሙሉ ሙሉ ለሙሉ ነጻ መደረጋቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ እንዳሳወቁት የመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ማሻሻያው ከነሐሴ 28/2013 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ተግባራዊ ይሆናል።
በዚህም መሠረት የምግብ ዘይት፣ ስኳርና ሩዝ ከውጭ ሲገቡም ሆነ በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸምባቸው ከቀረጥና ታክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ ሲሆኑ ስንዴ ከውጭ ሲገባ ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲሆን ተወስኗል።
ፓስታ እና ማኮሮኒ ከውጭ ሲገቡም ሆነ በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸም ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም የዶሮ እንቁላል ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ እንዲሆን መወሰኑን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ሚኒስትር ዲኤታው ጨምረውም መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠርና የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም ለማሳደግ የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንዲሁም አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን ተናግረዋል።
ይህ እርምጃ ተግባራዊ ሲደረግ መንግሥት በብዙ ቢሊዮን የሚገመት ገቢ እንደሚያጣ አመልክተው የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር በታክስ ብቻ የሚፈለገውን ውጤት ስለማያመጣ አቅርቦትን ለመጨመር መንግሥት በከፍተኛ ወጪ ሸቀጦችን በመግዛት በዝቅተኛ ዋጋ ለኅብረተሰቡ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች በሌሎች አካላት የሚገባውን አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ ይጨምር ዘንድ ለስድስት ወር ተፈቅዶ የነበረው ያለውጭ ምንዛሬ ሸቀጦችን የማስገባት አስራር ለሌላ ተጨማሪ ስድስት ወራት እንዲራዘም መደረጉንም ጨምረው ገልጸዋል።
እነዚህ ማሻሻያዎች የዋጋ ንረት በህብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ፣ በምግብ ዋጋ ላይ የሚከሰተውን ጭማሬ መንግሥት ለመቆጣጠር እንዲረዳውና ከውጭ እቃ ለሚያስገቡ ነጋዴዎችንም ለማበረታት ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።
በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ያለው የምግብ ዋጋ ግሽበት ባለፈው ወር 32 በመቶ የደረሰ ሲሆን ይህም በአሥር ዓመታት ውስጥ ከፍተኛው ነው ተብሏል።












