በሙስሊም አሜሪካውያን የምትመራው የአሜሪካ ከተማ

በሐምትራምክ የሚገኝ ስዕል

በአሜሪካዋ ሚቺጋን ግዛት በምትገኘው ሐምትራምክ ዋና ጎዳና መረማመድ በዓለም ያሉ ከተሞችን እንደጎበኙ የሚያደርግ ስሜትን ይፈጥራል።

ከተማዋን ያደመቁት የፖላንድ የቋሊማ መሸጫ መደብር፣ የምሥራቅ አውሮፓ ዳቦ ቤት፣ የየመን መገበያያ መደብር እና የቤንጋሊ ልብስ ቤት ከተማዋን የበርካታ ሕዝቦችና ባህሎች መናኸሪያ አድርገዋታል።

የቤተ ክርስቲያን ደወልና የሙስሊሞች የፀሎት ጥሪ (አዛን) በተመሳሳይ ወቅት ይሰሙባታል።

"ዓለምን በሁለት ስኩዌር ማይል" በሚል መፈክሯ የምትታወቀው ሐምትራምክ በአምስት ስኩዌር ኪሎሜትር የቆዳ ስፋቷ ውስጥ ወደ 30 የሚጠጉ ቋንቋዎች የሚነገሩባት በመሆን እውነትም "ትንሿ ዓለም" የሚል ስያሜ አሰጥቷታል።

በመካከለኛውም ምዕራብ የምትገኘውና የ28ሺህ ሕዝብ መኖሪያ የሆነችው ይህች ከተማ በዚህ ወር ደግሞ በታሪኳ ለየት ጉዳይ ተሰምቶባታል።

በሐምትራምክ ሁሉም አባላት የእስልምና ተከታይ የሆኑበት የከተማ ምክር ቤትና የሙስሊም ከንቲባ መርጣለች። በአሜሪካ ውስጥ የሙስሊሞች አስተዳደር ሲመሰረት ይህ የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን ታሪካዊ ክስተት ነው ተብሏል።

በአንድ ወቅት በከተማይቱ የሚደርስባቸውን መድሎና መገለል ሲታገሉ የነበሩት ሙስሊም ነዋሪዎች የዚህች የብዙ ባህሎች መናኸሪያ ከተማ ዋና አካል ሆነዋል፤ ከሕዝቡም ከግማሽ በላይ የሚሆነውንም ቁጥር ይዘዋል።

ምንም እንኳን ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች እና ከፍተኛ የባህል ክርክሮች ቢኖሩም፣ ሐምትራምክ ከተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ መሰረቶች የመጡ ነዋሪዎች ተስማምተው አብረው የሚኖሩባት ሆናለች።

ይህም በአሜሪካ ውስጥ እየጨመረ ለመጣው ብዝኃነት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ትርጉም ያለው የጥናት መነሻም ልትሆን እንደምትችል ተነግሯል።

ሆኖም በሐምትራምክ ያለው ታሪካዊ ክስተት በሌሎች የሚደገም ወይስ የተለየ ሆኖ የሚቀር የሚል ጥያቄም እያጫረ ነው።

Presentational grey line

በበርካታ የጀርመን ሰፋሪዎች ጥንታዊ ታሪኳ የሚጀምረው የሐምትራምክ ከተማ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በርካታ ሙስሊሞች የሚኖሩባት ስትሆን ይህ ከጥንት እስካሁን ያለው ገፅታዋም በጎዳናዎቿ ባሉ ኪነ ጥበቦች በግልፅ ይንጸባረቃል።

መደብሮቿ በአረብኛና በቤንጋሊ ቋንቋዎች በተጻፉ ስሞች ያጌጡ ሲሆን፣ የባንግላዴሽ ባለ ጥልፍ አልባሳት፣ ከየመን የመጣው አጭር ጥምዝ ቢላ (ጃምቢያስ) በበርካታ መደብሮቿ መስኮቶች ውስጥ ይታያሉ።

የከተማዋ ሙስሊም ነዋሪዎች ፓክዝኪ የሚባለውን የፖላንድ ዶናት ለመግዛት ወረፋ ይዘውና ተሰልፈው ይታያሉ።

"አጫጭር ቀሚስ የለበሱና ሰውነታቸው በንቅሳት ያጌጠ እንዲሁም ሙሉ ፊታቸውንና ሰውነታቸውን የሚሸፍን ልብስ ለብሰው በተመሳሳይ መንገድ ሲሄዱ ማየት የተለመደ ነው። ይህ ሁሉ የኛ አካል ነው" በማለት በከተማዋ መሃል የካፌ ባለቤት የሆነው የቦስኒያ ስደተኛ ዝላታን ሳዲኮቪች ይናገራል።

በሐምትራምክ የሚገኝ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዲትሮይት በአብዛኛው የተከበበችው ሐምትራምክ በአንድ ወቅት የአሜሪካ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ማዕከል ነበረች።

የመኪና አምራቹ ጄኔራል ሞተርስ ፋብሪካ የሚገኘውም በከተማዋና 'ሞተር ሲቲ' ተብላ በምትጠራው ዲትሮይት ድንበር ላይ ነው።

የመጀመሪያው ካዲላክ ኤልዶራዶም መገጣጠሚያውን በሐምትራምክ በ1980ዎቹ ከፈተ።

በ20ዎቹ ክፍለ ዘመን የፓላንድ ስደተኞች በገፍ መግባታቸውን ተከትሎም ከተማዋ "ትንሿ ዋርሶ" የሚል ስያሜ አገኘች።

የፖላንድ ተወላጁ የቀድሞው የሮም ሊቃነ ጳጳስ ጆን ፖል በአውሮፓውያኑ 1987 በአሜሪካ ጉብኝት ካደረጉባቸው ከተሞች መካከል አንዷ ናት። በአውሮፓውያኑ 1970 አካባቢም የከተማዋ 90 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የፖላንድ ዝርያ ነበረው።

በእነዚያ አስርት ዓመታት ውስጥም የአሜሪካ የመኪና ምርት ኢንዱስትሪ ማሽቆልቆሉን ተከትሎ ወጣትና ሃብታም ፖላንድ አሜሪካውያን ኑሯቸውን ወደ ሌሎች ከተሞች ማድረግ ጀመሩ።

ይህ ለውጥም ሐምትራምክን በሚቺጋን ካሉ ግዛቶች በጣም ድሃ ከተሞች ውስጥ አንዷ አድርጓታል። ሆኖም በከተማው የነበረው የተመጣጠነ የመግዛት አቅም ስደተኞችን መሳብ ጀመረ።

ባለፉት 30 ዓመታት ሐምትራምክ በከፍተኛ ለውጥ ያለፈች ሲሆን ለአረብ እና ለእስያ ስደተኞች በተለይም ከየመን እና ከባንግላዴሽ ለመጡት ዋነኛ ተመራጭ ማረፊያ ሆናለች።

በአሁኑ ጊዜ ካሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ውስጥ 42 በመቶ የውጭ አገራት ተወላጆች ናቸው። ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የእስልምና እምነት ተከታዮች እንደሆኑ ይታመናል።

Presentational grey line

አዲስ የተመረጡትን የምክር ቤት አባላት አወቃቀርም በሐምትራምክ ያለውን ተለዋዋጭ የሥነ ሕዝብ ሁኔታ የሚያንጸባርቅ ነው።

የከተማው ምክር ቤት አባላት ሁለት ቤንጋሊ አሜሪካውያን፣ ሦስት የመን አሜሪካውያን እና እምነቷን ወደ እስልምና የቀየረች ፖላንዳዊ-አሜሪካዊ ናቸው።

68 በመቶ ድምጽ በማሸነፍ ኡመር ጋሊብ በአሜሪካ የመጀመሪያው የመን አሜሪካዊ ከንቲባ ሆነዋል።

"ክብር እና ኩራት ይሰማኛል፣ ነገር ግን ትልቅ ኃላፊነት እንደሆነ አውቃለሁ" በማለት የ41 አመቱ ከንቲባ ተናግረዋል።

በየመን አንዲት መንደር ውስጥ የተወለዱት የአሁኑ ከንቲባ ወደ አሜሪካ የመጡት በ17 ዓመታቸው ነው።

በወቅቱም ሐምትራምክ አቅራቢያ በሚገኝ ፋብሪካ ውስጥ የፕላስቲክ መኪና መለዋወጫም እንዲሰሩ ተቀጠሩ። በኋላም እንግሊዝኛ ተምረው በህክምና ባለሙያነት የተመረቁ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በጤና ባለሙያነት እያገለገሉ ይገኛሉ።

"የሐምትራምክ ሕዝቦች በመጡበት በራሳቸው ባህል ይኮራሉ። እንዋሃድ ካልን ልዩነታችንን እናጣለን። የእያንዳንዳንችንን ልዩነት እናከብራለን" ሲሉ በአሁኑ ወቅት ለከተማዋ ምክር ቤት አባል የተመረጡት የ29 ዓመቷ አማንዳ ጃክዝኮውስኪ ተናግረዋል።

አክለውም "እርስ በርሳችን ተቀራርበን ስንኖር በልዩነታችን ላይ ላለማተኮር እንገደዳለን" ብለዋል።

ሆኖም ሁሉ ነገር አልጋ ባልጋ እንዳልሆነ ለ15 ዓመታት ያህል በከንቲባነት ያገለገሉትና በቅርቡ የተተኩት ካረን ማጄውስኪ ይናገራሉ። "ትንሽ ቦታ ነው፤ ግጭቶችም አሉ" ይላሉ።

በተለይም በአውሮፓውያኑ 2004 የእስላማዊ የፀሎት ጥሪ (አዛን) በድምፅ ማጉያ በአደባባይ እንዲሰማ ድምጽ መሰጠቱን ተከትሎ ውጥረቶች ነግሰው ነበር። አንዳንድ ነዋሪዎች በመስጊድ አቅራቢያ ያሉ ቡና ቤቶችን መከልከል የአካባቢውን ኢኮኖሚ ይጎዳል ሲሉ ተከራክረዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አንዷ አማንዳ ጃክዝኮውስኪ

የፎቶው ባለመብት, Courtesy of Amanda Jaczkowski

የምስሉ መግለጫ, ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አንዷ አማንዳ ጃክዝኮውስኪ

ከስድስት ዓመት በፊትም በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ሙስሊም አብላጫውን የያዘበት ምክር ቤት ስታቋቁምም ከመላው ዓለም የተውጣጡ ሚዲያዎች ሁኔታውን ለመታዘብ ወደ ሐምትራምክ ጎረፉ።

አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ባወጧቸው ዘገባዎችም በርካታ ሙስሊሞች በመኖራቸው "ውጥረት የበዛባት" የሚል ምስልም ለመስጠት ሞክረዋል።

የብሔራዊ ቴሌቪዥን አቅራቢም የወቅቱን ከንቲባ ማጄውስኪን ከንቲባ መሆን ያስፈራቸው እንደሆነ ሁሉ ጠይቋል። ይባስ ብሎ ሙስሊሞች በሚቆጣጠሩት ምክር ቤት ውስጥ የሸሪዓ ሕጎች በሕዝቡ ላይ ሊጫኑ ይችላሉ የሚሉ አስተያየቶች ከአንዳንዶች ተነስቷል።

"በሐምትራምክ ነዋሪዎች ለእንደዚህ አይነት ንግግሮች ጆሯቸውን አይሰጡም" ይላሉ ማጄውስኪ።

የሐምትራምክ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ በመሆኑ በጣም የሚያስደስታቸው ጉዳይ ነው እናም አዲስ ነዋሪዎች ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ለሚረዱ ተወካዮች ድምፃቸውን ቢሰጡ "ተፈጥሯዊ" ነው በማለት ያስረዳሉ።

የአሜሪካ የሕዝብ ቆጠራ ቢሮ ስለ ሃይማኖት መረጃ ባይሰበስብም፣ ነገር ግን ፒው የተሰኘ የምርምር ማዕከል በአውሮፓውያኑ 2020 በአሜሪካ ውስጥ ወደ 3.85 ሚሊዮን የሚጠጉ ሙስሊሞች እንዳሉ ግምቱን አስቀምጧል። ይህም አሃዝ ከጠቅላላይ ሕዝቡ 1.1 በመቶ ያህል ነው።

በአውሮፓውያኑ 2040 እስልምና በአሜሪካ ውስጥ ከክርስትና በመቀጠል ሁለተኛ ተከታይ ያለው እምነት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ምንም እንኳን የሃይማኖቱ ተከታዮች ቁጥር እያደገ ቢሄድም ሙስሊሞች በአሜሪካ ውስጥ አሁንም ቢሆን ጥላቻ ይደርስባቸዋል።

ሙስሊሞች ጸሎት በማድረግ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካ ከደረሰው 9/11 ጥቃት ከሁለት አስርት ዓመታትም በኋላ በአገሪቱ ያሉ ሙስሊሞች እንዲሁም ሌሎች አረብ አሜሪካውያን ከፍተኛ ጥላቻን እያስተናገዱ ይገኛሉ።

የያኔው ዕጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በርካታ ሕዝባቸው ሙስሊም ከሆኑ አገሮች የሚመጡ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ሃሳብ ባቀረቡበት ወቅት ግማሹ ሙስሊም አሜሪካውያን መድልዎና መገለል እንደደረሰባቸው በአውሮፓውያኑ 2016 ለፒው ተናግረዋል።

በተጨማሪም ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሁሉም የሃይማኖት ቡድኖች መካከል ሙስሊሞች አሁንም ቢሆን በአሜሪካ ሕዝብ ዘንድ በአሉታዊ ሁኔታ ነው የሚታዩት።

ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አሜሪካውያን በግላቸው የእስልምና ተከታይ የሆኑ ሰዎችን ባያውቁም፣ እናውቃለን የሚሉ አሜሪካውያን በበኩላቸው እስልምና ከሌሎች ሃይማኖቶች በበለጠ ሁከትን ያበረታታል ብለው እንደማያስቡ ተናግረዋል።

ስለ እስልምናም ሆነ ሙስሊሞችን ማወቅ ከእስልምና ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥላቻዎች ትርጉም እንደሌላቸው የሐምትራምክ ከተማ ዋና ማሳያ ናት።

ሻሃብ አህመድ የ9/11 ጥቃትን ተከትሎ ለከተማው ምክር ቤት አባልነት ሲወዳደሩ ትልቅ ፈተና ነበር የገጠማቸው።

"ወደ አውሮፕላኑ ያልደረስክ 20ኛው ጠላፊ ነህ የሚሉ በራሪ ወረቀቶች በከተማዋ ሁሉ ተበትነው ነበር" ሲሉ ቤንጋሊ አሜሪካዊው ሻሃብ ተናግረዋል።

በአውሮፓውያኑ 2001 በተካሄደው ምርጫም ተሸነፉ። ሆኖም ተስፋ አልቆረጡም ከሁለት ዓመታት በኋላ በነበረው የምረጡኝ ዘመቻ እንቅስቃሴ የጎረቤቶቻቸውን በር እያንኳኩ ድምፅ ስጡኝ አሉ። የከተማዋም ነዋሪ ሰማቸው፣ ድምፅም ሰጣቸው በዚህም የሐምትራምክ የመጀመሪያው ሙስሊም ከንቲባም ሆነው ተመረጡ።

ሂጃብ የጠመጠመች ሴትን የሚያሳይ ምስል
የምስሉ መግለጫ, ሂጃብ የጠመጠመች ሴትን የሚያሳይ ምስል

በአውሮፓውያኑ 2017 የትራምፕ አስተዳደር በሙስሊም አገራት ላይ እገዳውን ሲጥል ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን ለመግለፅ ተሰብስበው በከተማዋ ወጥተዋል።

"በሐምትራምክ ውስጥ ለመኖር የሌሎች ሰዎችን ዕምነትና ባህልን ማክበር እንዳለብን በማሳወቅ አንድነታችን እንዲያጠናክር ረድቶናል" በማለት "ሐምትራምክ፣ ዩኤስኤ" የተሰኘ ፊልም በተባባሪ ዳይሬክተርነት የሰራው ራዚ ጃፍሪ ይናገራል።

በአገር አቀፍ ደረጃም ቢሆን ሙስሊም አሜሪካውያን በፖለቲካው ዘንድ ጎልተው የሚታዩ ሆነዋል። በአውሮፓውያኑ 2007 የሚኒሶታ ዲሞክራት ኪት ኤሊሰን የመጀመሪያው ሙስሊም የምክር ቤት አባል ሆኑ። በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ምክር ቤት አራት ሙስሊም አባላት አሉት ።

ባለፈው ወር በነበረው የሐምትራምክ ምርጫ በርካታ ነዋሪዎች በምርጫ ጣቢያዎች ፊት ለፊት ተሰብስበው ሰላምታ ሲለዋወጡ ብዙዎችም "መርጫለሁ" የሚል ወረቀት ሲያሳዩም ነበር።

"ሰዎችን አንድ ላይ ማሰባሰብ የአሜሪካዊነት መገለጫ ነው። አንደኛውም እሴታችን ነው" በማለት የሚናገሩት ጃክኮቭስኪ ስደተኞች በዲሞክራሲ ሂደት ውስጥ በመሳተፋቸው የነበራቸውንም ደስታ ገልጸዋል።

ነገር ግን እንደሌላው የአገሪቱ ክፍል በከተማው ውስጥ ከፍተኛ የባህል ክርክሮች መካሄዳቸው አልቀረም።

በሰኔ ወር የከተማው አስተዳደር የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች መለያ የሆነው ሰንደቅ አላማ በከተማው አዳራሽ ፊት ለፊት እንዲውለበለብ ሲፈቅድ አንዳንድ ነዋሪዎችን አስቆጥቷል።

በተጨማሪም በግል የንግድ ተቋማትና ቤቶች ውጭ የተሰቀሉ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ሰንደቅ አላማዎች ተቀዳደዋል።

ከነዚህም መካከል ከማጄውስኪ ልብስ መደብር ውጪ የተሰቀለው ሰንደቅ አላማም ተቀዶ ተጥሏል። ይህንንም ተከትሎም "ይህ ለሰዎች በጣም አስደንጋጭ መልዕክት ያስተላልፋል" ብለዋል።

ዕፀ ፋርስም (ማሪዋና) የውዝግብ መንስኤ ሆኗል። በሐምትራምክ የተከፈቱ ሦስት የዕጸ ፋርስ ማከፋፈያዎች በአንዳንድ የሙስሊም እና የፖላንድ-ካቶሊክ ማኅበረሰቦች ቁጣን ቀስቅሰዋል።

ሌሎች ነዋሪዎች በበኩላቸው በወግ አጥባቂ ሙስሊም ማኅበረሰቦች ውስጥ ያለው የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ማነስ እንዳሳሰባቸው ሲናገሩ ይሰማሉ።

በምርጫው ምሽት ተመራጩ ከንቲባ ጋሊብ ከድምፅ መስጫው በኋላ በደስታ በፈነጠዙና ባቅላቫና 'ክባብ' በሚያከፋፍሉ የመን አሜሪካውያን ተከበው ነበር። የከበቧቸው ከ100 በላይ ደጋፊዎች ሁሉም ወንዶች ናቸው።

በምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻቸው ውስጥ ሴቶች እንደተሳተፉ የሚናገሩት ከንቲባው ሆኖም በባህሉ መሰረት ፆታዎች አንዳይቀላቀሉ ተደርጓል። ምንም እንኳን ራሳቸውን እንደ አሜሪካዊ በሚያዩት ወጣቶች ዘንድ ይህንን ሃሳብ ቢገዳደሩትም ከንቲባው ባህሉ መቀጠል አለበት ይላሉ።

ሐምትራምክ ከዚህ ባለፈ ደግሞ በተበላሹ መሰረተ ልማቶችና ውስን በሆኑ የምጣኔ ሃብት ዕድሎች በርካታ ችግሮች ተደቅኖባታል። በበጋው የጣለው ከባድ ዝናብ የከተማውን የፍሳሽ ማስወገጃዎች ሞልቶ በርካታ ቤቶችን አጥለቅልቋል። ለመጠጥ የሚውለው ውሃ በኬሚካል መበከሉ ሁኔታውን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል።

የከተማዋ ግማሽ የሚጠጋው ሕዝብ የሚኖረው ከድህነት ወለል በታች ነው። እነዚህ ችግሮች ለአዲሱ የከተማ አስተዳደርም ለዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ አንገብጋቢ የቤት ሥራዎች ናቸው።

"በአብዛኛው ሙስሊም በሚበዛበት ከተማ ዲሞክራሲ ምን ዓይነት መልክ አለው? እንደሌላው ቦታ ሁሉ የተዘበራረቀ እና የተወሳሰበ ነው" ሲል ዘጋቢ ፊልም ሰሪው ጃፍሪ የተናገረ ሲሆን አክሎም "አሁን ያለው የደስታ ስሜት ሲቀዘቅዝ ሥራው መሰራት አለበት" በማለትም ያስረዳል።