ኢትዮጵያዊው 'ኤልቪስ' አለማየሁ እሸቴና ሌሎች ታላላቅ አፍሪካውያን የታጡበት 2021

በ2021 አመት ያጣናቸው ታላላቅ አፍሪካውያን

የፎቶው ባለመብት, Various

የአውሮፓውያኑ 2021 ዓመት ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀሩት በአሁኑ ወቅት በተሰናባቹ ዓመት ይህችን ዓለም የተሰናበቱ በአህጉሪቷ ፈር ቀዳጅ፣ በርካቶችን ያነሳሱ እንዲሁም በማወዛገብም ስመ ጥር የነበሩ አፍሪካውያንን እንዘክር።

በ2021 ካጣናቸው ውስጥ እስቲ የአስሩን ህይወትና አስተዋፅኦ በጥቂቱ እንቃኝ፡

Short presentational grey line

ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ (80)

በአድናቂዎቹ ዘንድ ኢትዮጵያዊው 'ኤልቪስ' የሚል ስያሜ ያገኘው አለማየሁ እሸቴ ወርቃማ ዘመን ተብሎ በሚጠራው በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘመን ስሙ የናኘ ነበር።

'ተማር ልጄ'፣ 'አዲስ አበባ ቤቴ' እና ሌሎች እንደ ብሔራዊ መዝሙር ሊቆጠሩ በሚችሉ ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ሙዚቃዎቹ በበርካቶች ዘንድ አይረሴ ስምን ተክሏል።

አለማየሁ እስከ ህይወቱም መጨረሻ ድረስ ከመድረክ አልወረደም። ከልጅነቱ ጀምሮ የኤልቪስን ሙዚቃ በመጫወት፣ እንዲሁም ተለቅ ካለ በኋላም ጄምስ ብራውን በሙዚቃ ህይወቱ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንዳሳረፈበት በአውሮፓውያኑ 2008 ከጋርዲያን ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሮ ነበር።

አለማየሁ እሸቴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አለማየሁ እሸቴ

"እንደ አሜሪካዊ ለብሼ ፀጉሬን አስረዝሜ [የኤልቪስ ፕሪስሊን] ጄይልሃውስሮክና ሌት ሚ ዩር ቴዲ ቤርን እዘፍን ነበር። አንዳንድ ጊዜም 'ስትሬንጀርስ ኢን ዘ ናይት' የሚለውንም እንዘፍናለን። ነገር ግን ታዋቂነቴ ጣራ የነካው አማርኛ ዘፈኖችን መዝፈን በጀመርኩበት ወቅት ነው" ብሏል።

ለንደን ተቀማጭነቱን ያደረገው የሙዚቃ አሳታሚ ራፍ ትሬድ በአለማየሁ እሸቴ አንደኛው አልበም ላይ ባሰፈረው ማስታወሻ "አድማጮቹን ወደ ሙዚቃው ለማስገባት አይዘፍንም ነበር። ራሱን ሙዚቃ ውስጥ በጥልቀት ከትቶ አድናቂዎቹንም ሆነ ራሱን በሙዚቃ ስሜት በመመሰጥ ሌላ ዓለም ውስጥ ይከታቸው ነበር" በሚል አስፍሯል።

በዚሁ ዓመት ከተለዩን ሙዚቀኞች ሌላኛዋ ከኦፔራ እስከ ጃዝ ባህላዊ ዘፈኖችን በመዝፈን የምትታወቀው ደቡብ አፍሪካዊት ሲቦንጊሌ ኩማሎ ትገኛለች።

ደቡብ አፍሪካዊ የጃዝ ትሮምቦን ሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች ጆናስ ግዋንግዋ፣ የማላዊ መንፈሳዊ እና የጃዝ ሙዚቀኛ ዋምባሊ ምካንዳዊሬ፣ ከሴኔጋል ታዋቂ ዘፋኞች አንዱ ቲዮን ሴክ፣ የካሜሮን ዘፋኝ አንዱ ዌዝ ማዲኮ፣ በአደንዛዥ ዕፅ ምክንያት በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው ሩዋንዳዊው ራፐር ጄይ ፖሊ ህይወታቸው አልፏል።

በተጨማሪም በናሚቢያ የሂፕ ሆፕ ሙዚቃ ፈር ቀዳጅ የሚባለው ካኒባል እና ከአልጄሪያ በጣም ተወዳጅ ሙዚቀኞች ራባህ ዴሪሳ ህይወቱ ያለፈው በዚህ ዓመት ነው።

የአካባቢው አስተማሪ ሳራ ኦባማ (99)

ሳራ ኦባማ- የቀድሞ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የእንጀራ አያት ናቸው። ባራክ ኦባማ በአውሮፓውያኑ 2009 የአሜሪካ ፕሬዚዳንትነትን ሥልጣን ሲቆናጠጡ ስማቸው ገነነ።

ነገር ግን ማማ ሳራ በትውልድ አካባቢያቸው ምዕራብ ኬንያ ስመ ጥር ናቸው። ባህልም እንደሚያዘው ወደ ትዳር ዓለም የገቡት ገና በታዳጊነታቸው ሲሆን ያገቡትም ሰው ከእሳቸው በእድሜ በጣም የሚበልጥ ነበር።

ሳራ ኦባማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሳራ ኦባማ

ለብዙ አስርት ዓመታት ወላጅ አልባ ሕፃናትን እና ልጃገረዶችን ለማስተማር ፋውንዴሽን አቋቁመው ነበር። እሳቸው ማንበብ ባለመቻላቸው የሚቆጩት ማማ ሳራ የሴት ልጅ ትምህርት በውስጣቸው በከፍተኛ ሁኔታ የሚያንገበግባቸው ጉዳይ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2014 ባበበረከቱት የበጎ ሥራ አስተዋፅኦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት ፈር ቀዳጅነት ሽልማት አግኝተዋል።

ባራክ ኦባማ ለትምህርት "ያላት ቁርጠኝነት በልጆቿ ነው የተጀመረው" ይላሉ ስለ አያታቸው ሲናገሩ። "የወለደችው እናቱ ባትሆንም፣ አያቴ አባቴን እንደ ራሷ ልጅ አድርጋ አሳድጋለች። በእሷም ፍቅርና ማበረታቻ ነው የተጋረጡበትን ችግሮችና መሰናክሎች ጥሶ በአሜሪካ የነፃ ትምህርት እድል አግኝቶ ዩኒቨርስቲ ለመግባት የበቃው" ብለዋል።

ሳራ ኦባማ በህይወት ዘመናቸው በርካታ ለውጦችን አይተዋል "ነገር ግን ሁልጊዜም ቢሆን መንፈሷ ጠንካራ፣ ኩሩ፣ ታታሪ፣ በሰዎች የኑሮ መቀያየር የማያስደንቃት፣ በማስተዋል የተሞላች፣ ቀልደኛና በጭራሽ የማትቀየር ሰው ነበረች" ሲሉ ኦባማ መስክረዋል።

ኮቪድ ተጠራጣሪው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ (61)

የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ከሁለት ሳምንት በላይ በአደባባይ ሳይታዩ ቆይተው በመጋቢት ወር ህይወታቸው ማለፉ ተነግሯል።

የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ

የታንዛኒያ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ተጠራጣሪው ፕሬዚዳንት በልብ ችግሮች ህይወታቸው ማለፉን ገልጿል፣ ነገር ግን አንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግን በኮቪድ-19 እንደተያዙ ተናግረዋል ።

ከተራ ገበሬ የተወለዱት ማጉፉሊ በአንዳንድ አወዛጋቢ አቀራረባቸው ታዋቂነትን ያተረፉ ሲሆን ወደ ሥልጣንም የመጡት በአውሮፓውያኑ 2015 ነው።

ፕሬሱ ላይ ከፍተኛ ጭቆና በማድረግ፣ ተቃዋሚዎችን በማስፈራራት ቡልዶዘር የሚል የቅፅል ስም ያገኙት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከኮሮናቫይረስ ጋር የሚደረገውን ትግል በማዳከም በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሞት ምክንያት ሆነዋል በሚልም ክስ ይቀርብባቸዋል።

የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ባለሙያዋ ማቶላሴ ምቶንጋ (34)

የዛምቢያ ጥቂት የፕላስቲክ ቀዶ ሐኪሞች መካከል አንዷ የሆነችው ማቶላሴ ምቶንጋ በሕክምና ተማሪነቷ ወቅት በእሳት የተቃጠሉ ሕመምተኞችን በመንከባከብ ነው የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ጉዞዋ የጀመረው።

የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ባለሙያዋ ማቶላሴ ምቶንጋ

የፎቶው ባለመብት, ReSurge

የምስሉ መግለጫ, የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ባለሙያዋ ማቶላሴ ምቶንጋ

"በእርግጥ ፈር ቀዳጅነት ምን ማለት እንደሆነ በተግባር ያሳየች ግለሰብ ናት። በመላው ዛምቢያ የሰውን አካል መልሶ በመገንባት የተሃድሶ ህክምና ላይ የመጀመሪያዋ ለመሆን መንገድ ላይ ነበረች። ይህ በአካል ለሚያውቋት ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም የተሃድሶ ህክምና ላይ በአገሯም ሆነ በአጠቃላይ ለዓለም አሳዛዥ ኪሳራ ነው" በማለት መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት ሪ ሰርጅ ጽፏል።

ማቶላሴ በአሜሪካ የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ጉባኤን ተከታትላ ከተመለሰች ብዙም ሳይቆይ ህይወቷ አልፏል። "ዶክተር ምቶንጋ ከእራሷ ኪስ በማውጣት የባለቤቴን ቀጅ እጅ ፈውሳለታላች" በማለት ባለቤቱን ያከመቻት አንድ ግለሰብ በፌስቡክ ላይ ፅፏል።

የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ዴዝሞንድ ቱቱ ( 90)

በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ የተወለዱት ዴዝሞንድ ቱቱ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያንን ተቀላቅለው በአውሮፓውያኑ 1986 የመጀመሪያው ጥቁር የኬፕታውን ሊቀ ጳጳስ ለመሆን በቅተዋል ።

ጨቋኙንና የጥቂት ነጮች አገዛዝን ለማስወገድ በተደረገው ትግል የኖቤል የሰላም ሽልማት ከተሸለሙ ከሁለት ዓመታት በኋላም ነው የጵጵስናው ማዕረግ የተሰጣቸው።

የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ዴዝሞንድ ቱቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ዴዝሞንድ ቱቱ

በፍቅር አባ (ጳጳሱ) ተብለው የሚጠሩት ዴዝሞንድ ቱቱ በአውሮፓውያኑ 1994 ኔልሰን ማንዴላ በአገሪቱ የተካሄደውን የመጀመሪያውን ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ ካሸነፉ በኋላ የአገሪቱን የእውነት እና የዕርቅ ኮሚሽን እንዲመሩ ሊቀ መንበር ሆነው ተመረጡ።

እንደ ደቡብ አፍሪካ የሞራል አቅጣጫ መሪ ተደርገው የሚቆጠሩት ዴዝሞንድ ቱቱ አንዳንድ ጊዜም "የቀስተ ደመና አገር ብለው የሚጠሯትን" ደቡብ አፍሪካ፣ ድኅረ አፓርታይዱን አመራር በሰላ ትችት በመሸንቆጥ ይታወቃሉ።

ታዋቂው ሰባኪ ቲቢ ጆሹዋ ( 57)

በሰኔ ወር በናይጄሪያው ፓስተር የፌስቡክ ገጽ ላይ የወጣ ጽሑፍ "እግዚአብሔር አገልጋዩን ወሰደ" በሚል የሰባኪውን ሞት አሳውቋል።በመላው ዓለም የሚገኙና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የጆሹዋ ቸርች ኦፍ ኦል ኔሽንስ ቤተክርስቲያን ተከታዮችንም ያሳዘነ ጉዳይ ነበር።

ቲቢ ጆሹዋ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ቲቢ ጆሹዋ

ከተከታታዮቻቸው መካከል ታላላቅ ፖለቲከኞች እንደሚገኙበት የሚነገረው ተፅእኖ ፈጣሪው ሰባኪ በተአምራታቸው የሚታወቁ ሲሆን ኤችአይቪን ጨምሮ ሁሉንም አይነት በሽታዎች እንደሚፈውሱም ተናግረዋል።

አትሌት አግነስ ቲሮፕ (25)

የኬንያ አትሌቶች ጓደኛቸው እና የዓለም ክብረ ወሰንን የጨበጠችው አትሌት አግነስ ቲሮፕ በጥቅምት ወር በስለት ተወግታ መሞቷን መስማት ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ከተታቸው።

አትሌት አግነስ ቲሮፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አትሌት አግነስ ቲሮፕ

ባለቤቷ ኢብራሂም ሮቲች በግድያዋ ጥፋተኛ አይደለሁም ብሏል። አግነስ በመስከረም ወር በሴቶች 10 ኪሎ ሜትር የዓለም ክብረወሰንን የሰበረች እና በቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይም የተሳተፈች ተስፈኛ የርቀት ሯጭ ነበረች።

ሊቋጭ ቀናት በቀሩት አውሮፓውያኑ ዓመት ከአግነስ በተጨማሪ ኤርትራዊቷ ብስክሌተኛ ደስታ ኪዳኔ በስልጠና ላይ እያለች በመኪና ተገጭታ ህይወቷ አልፏል።

ንጉ ጉድ ዊል ዝዌሊቲኒ (72)

በደቡብ አፍሪካ የዙሉ ሕዝብ መሪ ንጉሥ ጉድ ዊል ዝዌሊቲኒ ህይወታቸው አልፏል። ንጉሡ በ50 ዓመት የግዛት ዘመናቸው ሁሉ የደቡብ አፍሪካ ባህል ማንነትን ለመጠበቅ ጠንካራ ተሟጋች ነበሩ።

ንጉስ ጉድ ዊል ዝዌሊቲኒ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ንጉስ ጉድ ዊል ዝዌሊቲኒ

አመጣጣቸው በአውሮፓያኑ 1879 ከእንግሊዝ ጦር ጋር በተደረገው ጦርነት ዙሉን የመራው የንጉሥ ሴትሽዋዮ ዘርም ይመዘዛል።

ንጉሡ ከስድስት ባለቤቶች 28 ልጆች ያሏቸው ሲሆን መደበኛ የፖለቲካ ሥልጣን ባይኖራቸው፣ ደቡብ አፍሪካ ዘመናዊ ብትሆንም የጥንት ባህሏንም አልተወችም የሚለውን እሳቤ ወካይ ናቸው ይባላል።

ከባለቤቶቻቸው መካከል ንግሥት ማንትፎምቢ ድላሚኒ-ዙሉ በመጋቢት ወር እንደ አስተዳዳሪነት ሥልጣኑን ቢረከቡም ከአንድ ወር በኋላ ህይወቷ አልፏል።

ተዋናይት ሶሄር ኤል-ባቢ ( 86)

ግብፃዊቷ ተዋናይት ሶሄር ኤል ባቢ በፊልም፣ በመድረክ እና በቴሌቭዥን ትወናዎቿ ለአምስት አስርት ዓመታት ያህል በመድረክ ላይ ቆይታለች። ምንም እንኳን በበርካታ ድራማዎች ላይ ብትተውንም ነገር ግን በአስቂኝ ችሎታዎቿ በጣም የምትታወቅ እና የተወደደች ነበረች።

ተዋናይት ሶሄር ኤል-ባቢ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ተዋናይት ሶሄር ኤል-ባቢ

ለአንዳንዶች የኤል-ባቢሊ ስም የግብፅ ሲኒማ ወርቃማ ዘመን ተብሎ በሚጠራው በ1950ዎቹ እና 1960ዎቹ መለዮ ነው።

በኋላም የቤተሰብን የቀን ተቀን ህይወት በሚያስቃኘው ረመዳን በተባለው ተከታታይ የመሪነት ሚና በመጫወት እንዲሁም በሌሎች የቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልሞች ስኬትን ማትረፍ ችላለች።

የዛምቢያ መስራች አባት ኬኔት ካውንዳ (97)

በሰኔ ወር ህይወታቸው ያለፈው የዛምቢያ የነጻነት መሪ ከአፍሪካ መሪዎችና ቅኝ አገዛዝን ከተዋጉ የመጨረሻዎቹ ትውልዶች አንዱ ነበሩ።

የዛምቢያ መስራች አባት ኬኔት ካውንዳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዛምቢያ መስራች አባት ኬኔት ካውንዳ

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ምኞታቸው ዛምቢያውያን በየማለዳው ለቁርስ በገበታቸው ላይ እንቁላል፣ ወተት እንዲሁም እያንዳንዱ ዛምቢያዊ ጫማ እንዲኖረው ነበር።

ኬኬ በመባል በቅፅል ስማቸው የሚታወቁት ኬኔት ካውንዳ ጊታር መጫወት ይወዱ ነበር።

ከቅኝ ግዛት ባርነት ለመላቀቅ በሚደረገው ትግል ከአገራቸው አልፈው በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓትን ለማስወገድ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው እንዲሁም በሞዛምቢክ እና በዚምባብዌ የነበሩ የነጻነት እንቅስቃሴዎችን ደግፈዋል።

ኬኔት ካውንዳ የነጻነት ትግሉን ከመቀላቀላቸውና በፊት የትምህርት ቤት መምህር ነበሩ።